መዝሙር 51

ለመዘምራን አለቃ፤ ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ።

2 ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤

3 እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና።

4 አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።

5 እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።

6 እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፤ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ።

7 በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ።

8 ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል።

9 ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ።

10 አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።

11 ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።

12 የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ።

13 ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፥ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።

14 የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከደም አድነኝ፥ አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች።

15 አቤቱ፥ ከንፈሮቼን ክፈት፥ አፌም ምስጋናህን ያወራል።

16 መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም።

17 የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።

18 አቤቱ፥ በውዴታህ ጽዮንን አሰማምራት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጽሮች ሥራ።

19 የጽድቁን መሥዋዕት መባውንም የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በወደድህ ጊዜ፥ ያን ጊዜ በመሠዊያህ ላይ ፍሪዳዎችን ይሠዋሉ።


መዝሙር 52

ለመዘምራን አለቃ፤ ኤዶማዊው ዶይቅ መጥቶ ለሳኦል። ዳዊት ወደ አቢሜሌክ ቤት መጥቶአል ብሎ በነገረው ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት።

1 ኃያል ሆይ፥ በክፋት ለምን ትጓደዳለህ? ሁልጊዜስ በመተላለፍ?

2 አንደበትህ ኃጢአትን ያስባል፤ እንደ ተሳለ ምላጭ ሽንገላን አደረግህ።

3 ከመልካም ይልቅ ክፋትን፥ ጽድቅንም ከመናገር ይልቅ ዓመፃን ወደድህ።

4 የሚያጠፉ ቃልን ሁሉ፥ የሽንገላ ምላስን ወደድህ።

5 ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ያፈርስሃል፤ ከቤትህም ይነቅልሃል ያፈልስሃልም፥ ሥርህንም ከሕያዋን ምድር።

6 ጻድቃን አይተው ይፈራሉ፤ በእርሱም ይሥቃሉ እንዲህም ይላሉ።

7 እግዚአብሔርን ረዳቱ ያላደረገ፥ በባለጠግነቱም ብዛት የታመነ፥ በከንቱ ነገርም የበረታ ያ ሰው እነሆ።

8 እኔስ በእግዚአብሔር ቤት እንደ ለመለመ እንደ ወይራ ዛፍ ነኝ፤ ለዓለምና ለዘላለም በእግዚአብሔር ምሕረት ታመንሁ።

9 አድርገህልኛልና ለዘላለም አመሰግንሃለሁ፥ በቅዱሳንህም ዘንድ መልካም ነውና ስምህን ተስፋ አደርጋለሁ።


መዝሙር 53

ለመዘምራን አለቃ በማኽላት፤ የዳዊት ትምህርት።

1 ሰነፍ በልቡ። አምላክ የለም ይላል። ረከሱ በበደላቸውም ጐሰቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም።

2 የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ።

3 ሁሉ በደሉ፥ አብረውም ረከሱ፤ አንድ ስንኳ በጎን ነገር የሚያደርጋት የለም።

4 ሕዝቤን እንጀራ እንደሚበላ የሚበሉ ግፍ አድራጊዎች ሁሉ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም።

5 እግዚአብሔር የግብዞችን አጥንቶች በትኖአልና። በዚያ የሚያስፈራ ሳይኖር እጅግ ፈሩ፤ እግዚአብሔር ንቆአቸዋልና አሳፈርሃቸው።

6 መድኃኒትን ከጽዮን ለእስራኤል ማን በሰጠ! እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ ያዕቆብ ደስ ይለዋል እስራኤልም ሐሤት ያደርጋል።


መዝሙር 54

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ ዜፋውያን መጥተው ለሳኦል። እነሆ ዳዊት በእኛ ዘንድ ተሸሽጓል ብለው በነገሩት ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት።

1 አቤቱ፥ በስምህ አድነኝ፥ በኃይልህም ፍረድልኝ።

2 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ የአፌንም ቃል አድምጥ፤

3 እንግዶች ቁመውብኛልና፥ ኃያላንም ነፍሴን ሽተዋታልና። እግዚአብሔርን በፊታቸው አላደረጉትም።

4 እነሆ፥ እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ ጌታዬም ለነፍሴ ደጋፊዋ ነው።

5 ክፋትን ወደ ጠላቶቼ ይመልሳታል፤ በእውነትህም አጥፋቸው።

6 ከፈቃዴ እሠዋልሃለሁ፤ አቤቱ፥ መልካም ነውና ስምህን አመሰግናለሁ፤

7 ከመከራ ሁሉ አድኖኛልና፥ ዓይኔም በጠላቶቼ ላይ አይታለችና።


መዝሙር 55

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የዳዊት ትምህርት።

1 አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ ልመናዬንም ቸል አትበል።

2 ተመልከተኝ ስማኝም። በኀዘኔ ተቅበዘበዝሁ ተናወጥሁም፤

3 ከጠላት ድምፅ ከዓመፀኛም ግፍ የተነሣ፤ ዓመፃን በላዬ ጥለውብኛልና፥ በቁጣም ጠልተውኛልና።

4 ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፥ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ።

5 ፍርሃትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ፥ ጨለማም ሸፈነኝ።

6 በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ!

7 እነሆ፥ ኰብልዬ በራቅሁ በምድረ በዳም በተቀመጥሁ፤

8 ከዐውሎና ከብርቱ ንፋስ ሸሽቼ በፈጠንሁ አልሁ።

9 አቤቱ፥ ግፍንና ጠብን በከተማ ውስጥ አይቼአለሁና አስጥማቸው እንደበታቸውንም ቍረጥ።

10 በቀንና በሌሊት በቅጥርዋ ይከብቡአታል፤ ዓመፃና ድካም ኃጢአትም በመካከልዋ ነው፤


መዝሙር 56

ለመዘምራን አለቃ፤ ከቅዱሳን ስለ ራቁ ሕዝብ፤ ፍልስጥኤማውያን በጌት በያዙት ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ።

1 አቤቱ፥ ሰው ረግጦኛልና ማረኝ፤ ሁልጊዜም በሰልፍ አስጨንቆኛል።

2 የሚዋጉኝ በዝተዋልና ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ጠላቶቼ ረገጡኝ።

3 እኔ ግን ፈራሁ በአንተም ታመንሁ።

4 በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፤ በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?

5 ሁልጊዜ ቃሎቼን ያጸይፉብኛል፤ በእኔ ላይም የሚመክሩት ሁሉ ለክፉ ነው።

6 ይሸምቁብኛል ይሸሽጉኝማል፥ እነርሱም ተረከዜን ይመለካከታሉ፥ ሁልጊዜም ነፍሴን ይሸምቁባታል።

7 በምንም ምን አታድናቸውም፤ አሕዛብን በቍጣ ትጥላቸዋለህ።

8 አምላክ ሆይ፥ ሕይወቴን ነገርሁህ፤ እንባዬን እንደ ትእዛዝህ በፊተህ አኖርህ።

9 በጠራሁህ ጊዜ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ አንተ አምላኬ እንደ ሆንህ እነሆ፥ አወቅሁ።

10 በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፤ በእግዚአብሔር ቃሉን አከብራለሁ።

11 በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል?

12 አቤቱ፥ የምስጋና ስእለት የምሰጥህ ከእኔ ዘንድ ነው፤

13 ነፍሴን ከሞት፥ እግሮቼን ከመውደቅ አድነሃልና፥ በሕያዋን ብርሃን እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው ዘንድ።


መዝሙር 57

ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በዋሻ በነበረበት ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ።

1 ማረኝ፥ አቤቱ፥ ማረኝ፥ ነፍሴ አንተን ታምናለችና፤ ጉዳት እስክታልፍ ድረስ በክንፎችህ ጥላ እታመናለሁ።

2 ወደሚረዳኝ እግዚአብሔር ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጮኻለሁ።

3 ከሰማይ ልኮ አዳነኝ፥ ለረገጡኝም ውርደትን ሰጣቸው፤ እግዚአብሔር ቸርነቱንና እውነቱን ላከ።

4 ነፍሴን ከአንበሶች መካከል አዳናት። ደንግጬ ተኛሁ፤ የሰው ልጆች ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ፥ አንደበታቸው የተሳለ ሾተል ነው።

5 አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።

6 ለእግሮቼ ወጥመድን አዘጋጁ፥ ነፍሴንም አጐበጡአት፤ ጕድጓድ በፊቴ ቈፈሩ፥ በእርሱም ወደቁ።

7 ልቤ ጨካኝ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጨካኝ ነው፤ እቀኛለሁ፥ እዘምራለሁ።

8 ክብሬ ይነሣ፥ በገናና መሰንቆም ይነሡ፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ።

9 አቤቱ፥ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ በወገኖችም ዘንድ እዘምርልሃለሁ፤

10 ምሕረትህ እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ብላለችና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ።

11 አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።


መዝሙር 58

ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። የዳዊት ቅኔ።

1 በእውነት ጽድቅን ብትናገሩስ፥ የሰው ልጆች ሆይ፥ በቅን ትፈርዳላችሁ፤

2 በልባችሁ በምድር ላይ ኃጢአትን ትሠራላችሁና፥ እጆቻችሁም ግፍን ይታታሉና።

3 ኅጥኣን ከማኅፀን ጀምረው ተለዩ፤ ከሆድም ጀምረው ሳቱ፥ ሐሰትንም ተናገሩ።

4 ቍጣቸው እንደ እባብ መርዝ ነው፥ እንደ ምድር አውሬም ጆሮዋ የተደፈነ ነው፥

5 አዋቂ ሲደግምባት የአስማተኛውን ቃል እንደማትሰማ።

6 እግዚአብሔር ጥርሳቸውን በአፋቸው ውስጥ ይሰብራል፤ እግዚአብሔር የአንበሶቹን መንጋጋቸውን ያደቅቃል።

7 እንደሚፈስስ ውኃ ይቀልጣሉ፤ እስኪያደክማቸው ድረስ ፍላጾቹን ይገትራል።

8 እንደሚቀልጥ ሰም ያልቃሉ፤ እሳት ወደቀች፥ ፀሐይንም አላዩአትም።

9 እሾኻችሁ ሳይታወቅ በትር ሆነ፤ ሕያዋን ሳላችሁ በመዓቱ ይነጥቃችኋል።

10 ጻድቅ በቀልን ባየ ጊዜ ደስ ይለዋል፤ በኃጢአተኛው ደምም እጁን ይታጠባል።

11 ሰውም። በእውነት ለጻድቅ ፍሬ አለው፤ በእውነት በምድር ላይ የሚፈርድ አምላክ አለ ይላል።


መዝሙር 59

ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። ሳኦል ይገድሉት ዘንድ ቤቱን እንዲጠብቁ በላከ ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ።

1 አምላኬ ሆይ፥ ከጠላቶቼ አድነኝ፤ በላዬም ከቆሙት አስጥለኝ።

2 ከግፍ አድራጊዎች ታደገኝ፥ ከደም ሰዎችም አድነኝ።

3 እነሆ፥ ነፍሴን ሸምቀውባታልና፥ ብርቱዎችም በላዬ ተሰበሰቡ። አቤቱ፥ በበደሌም አይደለም፥ በኃጢአቴም አይደለም።

4 ያለ በደል ሮጥሁ ተዘጋጀሁም፤ ተነሥ፥ ተቀበለኝ፥ እይም።

5 አንተም አቤቱ፥ የኃያላን አምላክ፥ የእስራኤል አምላክ፥ አሕዛብን ሁሉ ትጐበኛቸው ዘንድ ተነሥ፤ ዓመፅ የሚያደርጉትን ሁሉ አትማራቸው።

6 ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ።

7 እነሆ፥ በአፋቸው አሰምተው ይናገራሉ፤ ሰይፍም በከንፈሮቻቸው አለ፤ ማን ይሰማል? ይላሉ።

8 አንተ ግን አቤቱ፥ ትሥቅባቸዋለህ፥ አሕዛብንም ሁሉ ትንቃቸዋለህ።

9 እግዚአብሔር መጠጊያዬ ነውና ኃይሌን ወደ አንተ አስጠጋለሁ።

10 የአምላኬ ቸርነቱ ይገናኘኛል አምላኬ በጠላቶቼ ላይ ያሳየኛል።

11 ሕግህን እንዳይረሱ አትግደላቸው፤ አቤቱ ጋሻዬ፥ በኃይልህ በትናቸው አውርዳቸውም።

12 ስለ አፋቸው ኃጢአት ስለ ከንፈራቸውም ቃል፥ መርገምንና ሐሰትን ስለሚናገሩ፥ በትዕቢታቸው ይጠመዱ።

13 በቍጣ አጥፋቸው፥ እንዳይኖሩም አጥፋቸው፤ የያዕቆብም አምላክ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንዲገዛ ይወቁ።

14 ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ።

15 እነርሱም መብል ለመፈለግ ይበተኑ፤ ያልጠገቡ እንደ ሆነም ያንጐረጕራሉ።

16 እኔ ግን ለኃይልህ እቀኛለሁ፤ በምሕረትህም ማልዶ ደስ ይለኛል፤ በመከራዬ ቀን መጠጊያዬና አምባዬ ሆነኸኛልና።

17 ረዳቴ ሆይ፥ ለአንተ ለአምላኬ እዘምራለሁ፤ አንተ፥ አምላኬ፥ መጠጊያዬ ምሕረቴም ነህና።


መዝሙር 60

ለመዘምራን አለቃ፤ የሶርያን ሁለቱን ወንዞችና የሶርያን ሶባልን ባቃጠለ ጊዜ ኢዮአብም ተመልሶ ከኤዶማውያን ሰዎች በጨው ሸለቆ አሥራ ሁለት ሺህ በገደለ ጊዜ ለትምህርት የዳዊት ቅኔ።

1 አቤቱ፥ ጣልኸን አፈረስኸንም፤ ተቈጣኸን ይቅርም አልኸን።

2 ምድርን አናወጥሃት አወክሃትም፤ ተናውጣለችና ቍስልዋን ፈውስ።

3 ለሕዝብህ ጭንቅን አሳየሃቸው፥ አስደንጋጩንም ወይን አጠጣኸን።

4 ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው።

5 ወዳጆችህ እንዲድኑ በቀኝህ አድን፥ አድምጠኝም።

6 እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ፤ ደስ ይለኛል፥ ሴኬምንም እካፈላለሁ፥ የሱኮትንም ሸለቆ እሰፍራለሁ።

7 ገለዓድ የእኔ ነው፥ ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው። ይሁዳ ንጉሤ ነው፤

8 ሞዓብ መታጠቢያዬ ነው፥ በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እዘረጋለሁ፤ ፍልስጥኤም ይገዙልኛል።

9 ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል?

10 አቤቱ፥ የጣልኸን አንተ አይደለህምን? አምላክ ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም።

11 በመከራችን ረድኤትን ስጠን የሰውም ማዳን ከንቱ ነው።

12 በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን እርሱ የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋልና።


መዝሙር 61

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አምላክ ሆይ፥ ልመናዬን ስማ፥ ጸሎቴንም አድምጥ።

2 ልቤ ተስፋ በቈረጠ ጊዜ ከምድር ዳርቻ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ በድንጋይ ላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ።

3 ጽኑ ግንብ በጠላት ፊት ተስፋዬም ሆነኸኛልና መራኸኝ።

4 በድንኳንህ ለዘላለም እኖራለሁ፤ በክንፎችህም ጥላ እጋረዳለሁ፤

5 አቤቱ፥ አንተ ስእለቴን ሰምተሃልና፤ ስምህንም ለሚፈሩ ርስትህን ሰጠሃቸው።

6 ለንጉሥ ከቀን በላይ ቀን ትጨምራለህ፥ ዓመታቱም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሆናሉ።

7 በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ይኖራል፤ ይጠብቁት ዘንድ ምሕረትንና እውነትን አዘጋጅለት።

8 እንዲሁ ለስምህ ለዘላለም እዘምራለሁ ስእለቴን ሁልጊዜ እፈጽም ዘንድ።


መዝሙር 62

ለመዘምራን አለቃ፤ ስለ ኤዶታም፤ የዳዊት መዝሙር።

1 ነፍሴ ለእግዚአብሔር የምትገዛ አይደለችምን? መድኃኒቴ ከእርሱ ዘንድ ናትና።

2 እርሱ አምላኬ መድኃኒቴም ነውና፤ እርሱ መጠጊያዬ ነው፥ እጅግም አልታወክም።

3 እስከ መቼ በሰው ላይ ትቆማላችሁ? እናንተ ሁላችሁ እንዳዘነበለ ግድግዳ እንደ ፈረሰም ቅጥር ትገድላላችሁ።

4 ነገር ግን ክብሬን ይሽሩ ዘንድ መከሩ፥ ሐሰትንም ይወድዳሉ፤ በአፋቸው ይባርካሉ፥ በልባቸውም ይረግማሉ።

5 ነገር ግን፥ ነፍሴ ሆይ፥ አንቺ ለእግዚአብሔር ተገዢ፥ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ናትና።

6 እርሱ አምላኬ መድኃኒቴም ነውና፤ እርሱ መጠጊያዬ ነው፤ አልታወክም።

7 መድኃኒቴና ክብሬ በእግዚአብሔር ነው፤ የረድኤቴ አምላክ ተስፋዬም እግዚአብሔር ነው።

8 የሕዝብ ማኅበር ሁላችሁ፥ በእርሱ ታመኑ፥ ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ፤ እግዚአብሔር ረዳታችን ነው።

9 ነገር ግን የሰው ልጆች ከንቱ ናቸው፥ የሰው ልጆችም ሐሰተኞች ናቸው፤ በሚዛንም ይበድላሉ፥ እነርሱስ በፍጹም ከንቱ ናቸው።

10 ዓመፃን ተስፋ አታድርጉ፥ ቅሚያንም አትተማመኑት፤ ባለጠግነት ቢበዛ ልባችሁ አይኵራ።

11 እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፥ እኔም ይህን ብቻ ሰማሁ፤ ኃይል የእግዚአብሔር ነው፥

12 አቤቱ፥ ምሕረትም ያንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ፍዳውን ትሰጣለህና።


መዝሙር 63

በኤዶምያስ ምድረ በዳ በነበረ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አምላኬ፥ አምላኬ፥ ወደ አንተ እገሠግሣለሁ፤ ነፍሴ አንተን ተጠማች፥ ሥጋዬ አንተን እንዴት ናፈቀች እንጨትና ውኃ በሌለበት በምድረ በዳ።

2 ኃይልህንና ክብርህን አይ ዘንድ እንዲሁ በመቅደስ ውስጥ ተመለከትሁህ።

3 ምሕረትህ ከሕይወት ይሻላልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል።

4 እንዲህ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፥ በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ።

5 ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች፥ ከንፈሮቼም ስምህን በደስታ ያመሰግናሉ።

6 በመኝታዬም አስብሃለሁ፥ በማለዳም እናገርልሃለሁ፤

7 ረዳቴ ሆነኸኛልና፥ በክንፎችህም ጥላ ደስ ይለኛልና።

8 ነፍሴ በኋላህ ተከታተለች፥ እኔንም ቀኝህ ተቀበለችኝ።

9 እነርሱ ግን ነፍሴን ለከንቱ ፈለጓት፤ ወደ ምድር ጥልቅ ይገባሉ።

10 ለሰይፍ እጅ አልፈው ይሰጣሉ፥ የቀበሮም እድል ፈንታ ይሆናሉ።

11 ንጉሥ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤ በእርሱ የሚምል ሁሉ ይከብራል፥ ሐሰትን የሚናገር አፍ ይዘጋልና።


መዝሙር 64

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ወደ አንተ በለመንሁ ጊዜ ጸሎቴን ስማኝ፥ ከጠላትም ፍርሃት ነፍሴን አድን።

2 ከክፉዎች ሸንጎ ከዓመፀኞችም ብዛት ሰውረኝ።

3 እንደ ሰይፍ ምላሳቸውን አሰሉ፤ መራራ ነገርን ለማድረግ፥

4 ንጹሕንም በስውር ለመንደፍ ቀስትን ገተሩ፤ ድንገት ይነድፉታል አይፈሩምም።

5 ለእነርሱ ለራሳቸው ክፉ ነገርን አጸኑ፤ ወጥመድን ይሰውሩ ዘንድ ተማከሩ፤ ማንስ ያየናል? ይላሉ።

6 ዓመፃን ፈልጓት፥ ሲፈትኑም አለቁ፤ የሰው የውስጥ አሳቡና ልቡ የጠለቀ ነው፥

7 እግዚአብሔርም ከፍ ከፍ ይላል። የድንገትም ፍላጻ፤ ያቈስላቸዋል፤

8 አንደበታቸው ያሰናክላቸዋል፥ የሚያዩአቸውም ሁሉ ይደነግጣሉ።

9 ሰዎች ሁሉ ፈሩ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ ተናገሩ፥ ሥራውንም አስተዋሉ።

10 ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፥ በእርሱም ይታመናል፤ ልባቸውም የቀና ሁሉ እልል ይላሉ።


መዝሙር 65

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት የምስጋና መዝሙር።

1 አቤቱ፥ በጽዮን ለአንተ ምስጋና ይገባል፥ ለአንተም ጸሎት ይቀርባል።

2 ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል።

3 የዓመፃ ነገር በረታብን፤ ኃጢአታችንንስ አንተ ይቅር ትላለህ።

4 አንተ የመረጥኸው በአደባባዮችህም ለማደር የተቀበልኸው ምስጉን ነው፤ ከቤትህ በረከት እንጠግባለን።

5 ቤተ መቅደስህ ቅዱስ ነው በጽድቅም ድንቅ ነው። በምድር ዳርቻ ሁሉና በሩቅ ባሕር ውስጥ ላሉ ተስፋቸው የሆንህ፥ አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፥ ስማን።

6 በጉልበትህ ተራሮችን አጸናሃቸው፥ በኃይልም ታጥቀሃል።

7 የባሕሩን ጥልቀት የሞገድንም ጩኸት ታናውጣለህ።

8 ከተአምራትህ የተነሣ አሕዛብ ይደነግጣሉ፥ በምድር ዳርቻም የሚኖሩ ይፈራሉ፤ የጥዋትንና የማታን መውጫ ደስ ታሰኛቸዋለህ።

9 ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፥ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔርን ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳለህና።

10 ትልምዋን ታረካለህ፥ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፥ ቡቃያዋንም ትባርካለህ።

11 በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።

12 የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ።

13 ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፥ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም።


መዝሙር 66

ለመዘምራን አለቃ፤ የመነሣት የምስጋና መዝሙር።

1 በምድር ያላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፥

2 ለስሙም ዘምሩ፥ ለምስጋናውም ክብርን ስጡ።

3 እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት። ሥራህ ግሩም ነው፤ ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ።

4 በምድር ያሉ ሁሉ ለአንተ ይሰግዳሉ፥ ለአንተም ይዘምራሉ፥ ለስምህም ይዘምራሉ።

5 ኑ የእግዚአብሔርንም ሥራ እዩ፤ ከሰው ልጆች ይልቅ በምክር ግሩም ነው።

6 ባሕርን የብስ አደረጋት፥ ወንዙንም በእግር ተሻገሩ፤ በዚያ በእርሱ ደስ ይለናል።

7 በኃይሉ ለዘላለም ይገዛል፤ ዓይኖቹ ወደ አሕዛብ ይመለከታሉ፤ ዓመፀኞች ራሳቸውን ከፍ ከፍ አያድርጉ።

8 አሕዛብ ሆይ፥ አምላካችንን ባርኩ፥ የምስጋናውንም ድምፅ አሰሙ።

9 ነፍሴን በሕይወት ያኖራታል፥ እግሮቼንም ለመናወጥ አልሰጠም።

10 አቤቱ፥ ፈትነኸናልና፥ ብርንም እንደሚያነጥሩት አንጥረኸናልና።

11 ወደ ወጥመድ አገባኸን፥ በጀርባችንም መከራን አኖርህ።

12 በራሳችን ላይ ሰውን አስረገጥኸን፤ በእሳትና በውኃ መካከል አለፍን፥ ወደ ዕረፍትም አወጣኸን።

13-14 ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ በመከራዬ ጊዜ በአፌ የተናገርሁትን ከንፈሮቼም ያሉትን ስእለቴን ለአንተ እፈጽማለሁ።

15 ከዕጣንና ከወጠጤዎች ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ፍሪዳን አቀርባለሁ፤ ላሞችንና ፍየሎችን እሠዋልሃለሁ።

16 እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሁሉ፥ ኑ፥ ስሙኝ፤ ለነፍሴ ያደረገላትን ልንገራችሁ።

17 በአፌ ወደ እርሱ ጮኽሁ፥ በአንደበቴም አመሰገንሁት።

18 በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር።

19 ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማኝ፤ የልመናዬን ድምፅ አደመጠ።

20 ጸሎቴን ያልከለከለኝ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን።


መዝሙር 67

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ይማረን ይባርከንም፥ ፊቱንም በላያችን ያብራ፤

2 በአሕዛብ ሁሉ መካከል ማዳንህን፥ መንገድህንም በምድር እናውቅ ዘንድ።

3 አቤቱ፥ አሕዛብ ያመስግኑህ፥ አሕዛብ ሁሉ ያመስግኑህ።

4 ለአሕዛብ በቅን ትፈርድላቸዋለህና፥ አሕዛብንም በምድር ላይ ትመራለህና አሕዛብ ደስ ይበላቸው ሐሤትም ያድርጉ።

5 አቤቱ፥ አሕዛብ ያመስግኑህ፥ አሕዛብ ሁሉ ያመስግኑህ።

6 ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።

7 እግዚአብሔር ይባርከናል፥ የምድርም ዳርቻ ሁሉ ይፈሩታል።


መዝሙር 68

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት የምስጋና መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ይነሣ፥ ጠላቶቹም ይበተኑ፥ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ።

2 ጢስ እንደሚበንን እንዲሁ ይብነኑ፤ ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ ኅጥኣን ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ።

3 ጻድቃንም ደስ ይበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሐሤት ያድርጉ፥ በደስታም ደስ ይበላቸው።

4 ለእግዚአብሔር ተቀኙ ለስሙም ዘምሩ፤ ወደ ምድረ በዳ ለወጣም መንገድ አድርጉ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው፥ በፊቱም ደስ ይበላችሁ፤ በፊቱም ይደነግጣሉ።

5 እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው።

6 እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፤ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ።

7 አቤቱ፥ በሕዝብም ፊት በወጣህ ጊዜ፥ በምድረ በዳም ባለፍህ ጊዜ፥ ምድር ተናወጠች፥

8 ከሲና አምላክ ፊት፥ ከእስራኤል አምላክ ፊት ሰማያትም አንጠበጠቡ።

9 አቤቱ፥ የሞገስን ዝናብ ለርስትህ አዘነብህ፥ በደከመም ጊዜ አንተ አጸናኸው።

10 እንስሶችህ በውስጡ አደሩ፤ አቤቱ፥ በቸርነትህ ለድሆች አዘጋጀህ።

11 እግዚአብሔር ቃሉን ሰጠ፤ የሚያወሩት ብዙ ሠራዊት ናቸው።

12 የሠራዊት ነገሥታት ፈጥነው ይሸሻሉ፤ በቤትም የምትኖር ምርኮን ተካፈለች።

13 በርስቶች መካከል ብታድሩ፥ ከብር እንደ ተሠሩ እንደ ርግብ ክንፎች፥ በቅጠልያ ወርቅም እንደ ተለበጡ ላባዎችዋ ትሆናላችሁ።

14 ሰማያዊ ንጉሥ በላይዋ ባዘዘ ጊዜ፥ በሰልሞን ላይ በረዶ ዘነበ።

15 የእግዚአብሔር ተራራ የለመለመ ተራራ ነው፤ የጸና ተራራና የለመለመ ተራራ ነው።

16 የጸኑ ተራራዎች ለምን ይነሣሉ? እግዚአብሔር ይህን ተራራ ያድርበት ዘንድ ወደደው፤ በእውነት እግዚአብሔር ለዘላለም ያድርበታል።

17 የእግዚአብሔር ሰረገላዎች የብዙ ብዙ ሺህ ናቸው፤ ጌታ በመቅደሱ በሲና በመካከላቸው ነው።

18 ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ።

19 እግዚአብሔር አምላክ ቡሩክ ነው፤ እግዚአብሔር በየዕለቱ ቡሩክ ነው፤ የመድኃኒታችን አምላክ ይረዳናል።

20 አምላካችንስ የደኅንነት አምላክ ነው፤ ከሞት መውጣትም ከእግዚአብሔር ነው።

21 ነገር ግን እግዚአብሔር የጠላቶቹን ራስ፥ በኃጢአት የሚሄድንም የጠጕሩን አናት ይቀጠቅጣል።

22 እግዚአብሔር እንዲህ አለ። ከባሳን አመጣቸዋለሁ፥ ከባሕርም ጥልቅ እመልሳቸዋለሁ፥

23 እግሮችህ በደም ይረገጡ ዘንድ፥ የውሾችህ ምላስ በጠላቶች ላይ ይሆን ዘንድ።

24 የአምላኬ የንጉሥ መንገድ በመቅደሱ፥ አቤቱ፥ መንገድህ ተገለጠ።

25 አለቆች ቀደሙ፥ መዘምራንም ተከተሉ፤ ከበሮን በሚመቱ በቈነጃጅት መካከል።

26 እግዚአብሔርን በጉባኤ፥ ጌታችንንም በእስራኤል ምንጭ አመስግኑት።

27 ወጣቱ ብንያም በጕልበቱ በዚያ አለ፥ ገዦቻቸው የይሁዳ አለቆች የዛብሎን አለቆችና የንፍታሌምም አለቆች።

28 አቤቱ፥ ኃይልህን እዘዝ፤ አቤቱ፥ ይህንም ለእኛ የሠራኸውን አጽናው።

29 በኢየሩሳሌም ስላለው መቅደስህ ነገሥታት እጅ መንሻን ለአንተ ያመጣሉ።

30 በሸምበቆ ውስጥ ያሉትን አራዊት፥ በአሕዛብ ውስጥ ያሉትን የበሬዎችንና የወይፈኖችን ጉባኤ ገሥጽ፥ እንደ ብር የተፈተኑት አሕዛብ እንዳይዘጉ፤ ሰልፍን የሚወድዱትን አሕዛብን በትናቸው።

31 መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።

32 የምድር ነገሥታት፥ ለእግዚአብሔር ተቀኙ፥ ለጌታም ዘምሩ።

33 በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኃይል ቃል የሆነ ቃሉን፥ እነሆ፥ ይሰጣል።

34 ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ፤ ግርማው በእስራኤል ላይ፥ ኃይሉም በደመናት ላይ ነው።

35 እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፤ የእስራኤል አምላክ እርሱ ኃይልን ብርታትንም ለሕዝቡ ይሰጣል፤ እግዚአብሔርም ይመስገን።


መዝሙር 69

ለመዘምራን አለቃ፤ በመለከቶች፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ውኃ እስከ ነፍሴ ደርሶብኛልና አድነኝ።

2 በጥልቅ ረግረግ ጠለቅሁ መቋሚያም የለኝም። ወደ ጥልቅ ባሕር ገባሁ ማዕበልም አሰጠመኝ።

3 በጩኸት ደከምሁ ጕሮሮዬም ሰለለ፤ አምላኬን ስጠብቅ ዓይኖቼ ፈዘዙ።

4 በከንቱ የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጕር በዙ፤ በዓመፅ ያሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ በረቱ፤ በዚያን ጊዜ ያልቀማሁትን መለስሁ።

5 አቤቱ፥ አንተ ስንፍናዬን ታውቃለህ፥ ኃጢአቴም ከአንተ አልተሰወረም።

6 አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ ተስፋ የሚያደርጉህ በእኔ አይፈሩ፤ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ የሚሹህ በእኔ አይነወሩ።

7 ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፥ እፍረትም ፊቴን ሸፍናለችና።

8 ለወንድሞቼ እንደ ሌላ፥ ለእናቴ ልጆችም እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው፥

9 የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና።

10 ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፥ ለስድብም ሆነብኝ።

11 ማቅ ለበስሁ ምሳሌም ሆንሁላቸው።

12 በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ፤ ወይን የሚጠጡ እኔን ይዘፍናሉ።

13 አቤቱ፥ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወደ አንተ ነው፤ አቤቱ፥ በምሕረትህ ብዛት በማዳንህም እውነት አድምጠኝ።

14 እንዳይውጠኝ ከረግረግ አውጣኝ፤ ከሚጠሉኝና ከጥልቅ ውኃ አስጥለኝ።

15 የውኃው ማዕበል አያስጥመኝ፥ ጥልቁም አይዋጠኝ፥ ጕድጓድም አፉን በእኔ ላይ አይዝጋ።

16 አቤቱ፥ ምሕረትህ መልካም ናትና ስማኝ። እንደ ርኅራኄህም ብዛት ወደ እኔ ተመልከት፤

17 ከባሪያህም ፊትህን አትሰውር፤ ተጨንቄአለሁና ፈጥነህ አድምጠኝ።

18 ነፍሴን ተመልክተህ ተቤዣት፤ ስለ ጠላቶቼም አድነኝ።

19 አንተ ስድቤን እፍረቴንም ነውሬንም ታውቃለህ፤ የሚያስጨንቁኝ ሁሉ በፊትህ ናቸው።

20 ነፍሴ ስድብንና ኃሣርን ታገሠች፤ አስተዛዛኝም ተመኘሁ አላገኘሁም። የሚያጽናናኝም አጣሁ።

21 ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፥ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ።

22 ማዕዳቸው በፊታቸው ለወጥመድ ለፍዳ ለዕንቅፋት ትሁንባቸው፤

23 ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፥ ጀርባቸውም ዘወትር ይጕበጥ።

24 መዓትህን በላያቸው አፍስስ፥ የቍጣህ መቅሠፍትም ያግኛቸው።

25 ማደሪያቸው በረሃ ትሁን፥ በድንኳኖቻቸውም የሚቀመጥ አይገኝ፤

26 አንተ የቀሠፍኸውን እነርሱ አሳድደዋልና፥ በቍስሌም ላይ ጥዝጣዜ ጨመሩብኝ።

27 በኃጢአታቸው ላይ ኃጢአትን ጨምርባቸው፥ በጽድቅህም አይግቡ።

28 ከሕያዋን መጽሐፍ ይደምሰሱ፥ ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ።

29 እኔ ችግረኛና ቍስለኛ ነኝ፤ አቤቱ፥ የፊትህ መድኃኒት ይቀበለኝ።

30 የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አመሰግናለሁ፥ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።

31 ቀንድና ጥፍር ካበቀለ ከእምቦሳ ይልቅ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል።

32 ችግረኞች ያያሉ ደስ ይላቸዋል፤ እግዚአብሔርን ፈልጉ ሕያዋንም ሁኑ።

33 እግዚአብሔር ችግረኞችን ሰምቶአልና፥ እስረኞቹንም አልናቀምና።

34 ሰማይና ምድር ባሕርም በእርስዋም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመሰግኑታል።

35 እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና፥ የይሁዳንም ከተሞች ይሠራልና፤ በዚያም ይቀመጣሉ ይወርሱአትማል።

36 የባሪያዎቹ ዘር ይኖሩባታል። ስሙንም የሚወድዱ በዚያ ይቀመጣሉ።


መዝሙር 70

ለመዘምራን አለቃ፤ ለመታሰቢያ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ እኔን ለማዳን ተመልከት፤ አቤቱ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

2 ነፍሴን የሚሹአት ይፈሩ ይጐስቍሉም፥ ክፉንም የሚመክሩብኝ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይፈሩም።

3 እንኳ እንኳ የሚሉኝ አፍረው ወዲያው ወደ ኋላቸው ይመለሱ።

4 የሚሹህ ሁሉ በአንተ ሐሤት ያድርጉ ደስ ይበላቸው፤ ማዳንህን የሚወድዱ ሁልጊዜ። እግዚአብሔር ታላቅ ነው ይበሉ።

5 እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፤ አቤቱ፥ እርዳኝ፤ ረዳቴ ታዳጊዬም አንተ ነህ፤ አቤቱ፥ አትዘግይ።


መዝሙር 71

አስቀድመው ስለ ማረኩ ስለ አሚናዳብ ልጆች የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ አንተን ታመንሁ፤ ለዘላለም አልፈር።

2 በጽድቅህ አስጥለኝ ታደገኝም፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድነኝም።

3 በጠንካራ ቦታ ታድነኝ ዘንድ አምላክና መሸሸጊያ ሁነኝ፤ ኃይሌ መጠጊያዬ አንተ ነህና።

4 አምላኬ፥ ከኃጢአተኛ እጅ፥ ከዓመፀኛና ከግፈኛም እጅ አድነኝ።

5 አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፥ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና።

6 ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ፥ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤ ሁልጊዜም ዝማሬዬ ለአንተ ነው።

7 ለብዙዎች መደነቂያ ሆንሁ፤ አንተ ግን ብርቱ መጠጊያዬ ነህ።

8 አፌን ምስጋና ምላ ሁልጊዜ ክብርህንና ግርማህን እዘምር ዘንድ።

9 በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፥ ጕልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ።

10 ጠላቶቹ በላዬ ተናግረዋልና፤ ነፍሴንም የሚሹአት በአንድነት ተማክረዋልና፥ እንዲህም አሉ።

11 እግዚአብሔር ትቶታል፤ የሚያድነው የለምና ተከትላችሁ ያዙት።

12 አምላክ ሆይ፥ ከእኔ አትራቅ፤ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

13 ነፍሴን የሚቃወሙአት ይፈሩ ይጥፉም፥ ጕዳቴንም የሚፈልጉ እፍረትንና ኃሣርን ይልበሱ።

14 እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፥ በምስጋናህም ሁሉ ላይ እጨምራለሁ።

15 ሥራን አላውቅምና አፌ ጽድቅህን ሁልጊዜም ማዳንህን ይናገራል።

16 በእግዚአብሔር ኃይል እገባለሁ፤ አቤቱ፥ ጽድቅህን ብቻ አስባለሁ።

17 አምላኬ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እስከ ዛሬም ተአምራትህን እነግራለሁ።

18 እስካረጅም እስክሸመግልም ድረስ፥ ለሚመጣ ትውልድም ሁሉ ክንድህን ኃይልህንም ጽድቅህንም እስክነግር ድረስ፥ አቤቱ፥ አትተወኝ።

19 አቤቱ፥ እስከ አርያም ታላላቅ ነገሮችን አደረግህ፤ አምላክ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?

20 ብዙ ጭንቀትንና መከራን አሳይተኸኛልና፥ ተመለስህ ሕያውም አደረግኸኝ፤ ከምድር ጥልቅም እንደ ገና አወጣኸኝ።

21 ጽድቅህንም አብዛው፥ ተመልሰህም ደስ አሰኘኝ፥ ከጥልቅም እንደ ገና አወጣኸኝ።

22 እኔም በበገና ስለ እውነትህ አመሰግንሃለሁ፤ የእስራኤል ቅዱስ አምላክ ሆይ፥ በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ።

23 ዝማሬን ባቀርብሁልህ ጊዜ ከንፈሮቼ ደስ ይላቸዋል፥ አንተ ያዳንሃትም ነፍሴ።

24 ጕዳቴን የሚሹ ባፈሩና በተነወሩ ጊዜ አንደበቴ ደግሞ ሁልጊዜ ጽድቅህን ይናገራል።


መዝሙር 72

ስለ ሰሎሞን።

1 አቤቱ፥ ፍርድህን ለንጉሥ ስጥ፥ ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ፥

2 ሕዝብህን በጽድቅ፥ ችግረኞችህንም በፍርድ ይዳኝ ዘንድ።

3 ተራሮችና ኰረብቶች ለሕዝብህ ሰላምን ይቀበሉ።

4 ለችግረኞች ሕዝብ በጽድቅ ትፈርዳለህ የድሆችንም ልጆች ታድናለህ፤ ክፉውንም ታዋርደዋለህ።

5 ፀሐይ በሚኖርበት ዘመን ሁሉ፥ በጨረቃም ፊት ለፊት ለልጅ ልጅ ይኖራል።

6 እንደ ዝናብ በታጨደ መስክ ላይ፥ በምድርም ላይ እንደሚንጠባጠብ ጠብታ ይወርዳል።

7 በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፥ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው።

8 ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፥ ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይገዛል።

9 በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ።

10 የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ።

11 ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል። አሕዛብም ሁሉ ይገዙለታል።

12 ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፥ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና።

13 ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፥ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል።

14 ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው በፊቱ ክቡር ነው።

15 እርሱ ይኖራል ከዓረብም ወርቅ ይሰጡታል፤ ሁልጊዜም ወደ እርሱ ይጸልያሉ፥ ዘወትርም ይባርኩታል።

16 በምድር ውስጥ በተራሮች ላይ መጠጊያ ይሆናል፤ ፍሬውም ከሊባኖስ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፤ እንደ ምድር ሣር በከተማ ይበቅላል።

17 ስሙ ለዘላለም ቡሩክ ይሆናል፥ ከፀሐይም አስቀድሞ ስሙ ይኖራል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉ በእርሱ ይባረካሉም አሕዛብ ሁሉ ያመሰግኑታል።

18 ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ።

19 የምስጋናው ስም ለዓለምና ለዘላለም ይባረክ፤ ምስጋናውም ምድርን ሁሉ ይምላ። ይሁን፤ ይሁን።

20 የእሴይ ልጅ የዳዊት መዝሙር ተፈጸመ።


መዝሙር 73

የአሳፍ መዝሙር።

1 ልባቸው ለቀና ለእስራኤል እግዚአብሔር እንዴት ቸር ነው።

2 እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ።

3 የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና።

4 ለሞታቸው መጣጣር የለውምና፤ ኃይላቸውም ጠንካራ ነውና።

5 እንደ ሰው በድካም አልሆኑም፥ ከሰው ጋርም አልተገረፉም።

6 ስለዚህ ትዕቢት ያዛቸው፤ ኃጢአትንና በደልን ተጐናጸፉአት።

7 ዓይናቸው ስብ ስለ ሆነ ወጣ፤ ልባቸውም ከምኞታቸው ይልቅ አገኘ።

8 አስበው ክፉ ነገርን ተናገሩ። ከፍ ከፍ ብለውም በዓመፃ ተናገሩ።

9 አፋቸውን በሰማይ አኖሩ፥ አንደበታቸውም በምድር ውስጥ ተመላለሰ።

10 ስለዚህ ሕዝቤ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ ፍጹም ጊዜም በላያቸው ይገኛል፤

11 እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በልዑልስ ዘንድ በውኑ እውቀት አለ? ይላሉ።

12 እነሆ፥ እነዚህ ኃጢአተኞች ይደሰታሉ፥ ሁልጊዜም ባለጠግነታቸውን ያበዛሉ።

13 እንዲህም አልሁ። በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፥ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ።

14 ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው።

15 እንደዚህ ብዬ ብናገር ኖሮ፥ እነሆ፥ የልጆችህን ትውልድ በበደልሁ ነበር።

16 አውቅም ዘንድ አሰብሁ፥ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበረ።

17 ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፥ ፍጻሜአቸውንም እስካስተውል ድረስ።

18 በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፥ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው።

19 እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ።

20 ከሕልም እንደሚነቃ፥ አቤቱ፥ ስትነቃ ምልክታቸውን ታስነውራለህ።

21 ልቤ ነድዶአልና፥ ኵላሊቴም ቀልጦአልና፤

22 እኔ የተናቅሁ ነኝ አላውቅሁምም፥ በአንተ ዘንድም እንደ እንስሳ ሆንሁ።

23 እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ።

24 በአንተ ምክር መራኸኝ፤ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ።

25 በሰማይ ያለኝ ምንድር ነው? በምድርስ ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ?

26 የልቤ አምላክ ሆይ፥ ልቤና ሥጋዬ አለቀ፤ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም እድል ፈንታዬ ነው።

27 እነሆ፥ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና ከአንተ ርቀው የሚያመነዝሩትንም ሁሉ አጠፋኻቸው።

28 ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ መታመኛዬም እግዚአብሔር ነው በጽዮን ልጅ በሮች ምስጋናህን ሁሉ እናገር ዘንድ።


መዝሙር 74

የአሳፍ ትምህርት።

1 አቤቱ፥ ስለ ምን ለዘወትር ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቍጣህን ስለ ምን ተቈጣህ?

2 አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን፥ የተቤዤሃትንም የርስትህን በትር፥ በእርስዋ ያደርህባትን የጽዮንን ተራራ አስብ።

3 ጠላት በቅዱሳንህ ላይ እንደ ከፋ መጠን፥ ሁልጊዜም በትዕቢታቸው ላይ እጅህን አንሣ።

4 ጠላቶችህ በበዓል መካከል ተመኩ፤ የማያውቁትንም ምልክት ምልክታቸው አደረጉ።

5 እንደ ላይኛው መግቢያ ውስጥ በዱር እንዳሉም እንጨቶች፥ በመጥረቢያ በሮችዋን ሰበሩ።

6 እንዲሁ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰበሩአት።

7 መቅደስህን በእሳት አቃጠሉ፤ የስምህንም ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ።

8 አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው። ኑ፥ የእግዚአብሔርን በዓሎች ከምድር እንሻር አሉ።

9 ምልክታችንን አናይም ከእንግዲህ ወዲህም ነቢይ የለም፤ እስከ መቼ እንዲኖር የሚያውቅ በኛ ዘንድ የለም።

10 አቤቱ፥ ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል? ስምህን ጠላት ሁልጊዜ ያቃልላልን?

11 ቀኝህንም በብብትህ መካከል፥ እጅህንም ፈጽመህ ለምን ትመልሳለህ?

12 እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ።

13 አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት፤ አንተ የእባቦችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ።

14 አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።

15 አንተ ምንጮቹንና ፈሳሾቹን ሰነጠቅህ፤ አንተ ሁልጊዜ የሚፈስሱትን ወንዞች አደረቅህ።

16 ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው፤ አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ።

17 አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ፤ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ።

18 ይህን ፍጥረትህን አስብ። ጠላት እግዚአብሔርን ተላገደ፥ ሰነፍ ሕዝብም ስሙን አስቈጣ።

19 የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት፤ የችግረኞችህን ነፍስ ለዘወትር አትርሳ።

20 ወደ ኪዳንህ ተመልከት፥ የምድር የጨለማ ስፍራዎች በኅጥኣን ቤቶች ተሞልተዋልና።

21 ችግረኛ አፍሮ አይመለስ፤ ችግረኛና ምስኪን ስምህን ያመሰግናሉ።

22 አቤቱ፥ ተነሥ በቀልህንም ተበቀል፤ ሰነፎች ሁልጊዜም የተላገዱህን አስብ።

23 የባሪያዎችህን ቃል አትርሳ፤ የጠላቶችህ ኵራት ሁልጊዜ ወደ አንተ ይወጣል።


መዝሙር 75

ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። የአሳፍ የምስጋና መዝሙር።

1 አቤቱ፥ እናመሰግንሃለን እናመሰግንሃለን ስምህንም እንጠራለን፤ ተኣምራትህን ሁሉ እናገራለሁ።

2 ጊዜውን ስቀበል እኔ በቅን እፈርዳለሁ።

3 ምድርና በእርስዋ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ ቀለጡ፥ እኔም ምሰሶችዋን አጠናሁ።

4 ዓመፀኞችን። አትበድሉ አልኋቸው፥ ኃጢአተኞችንም። ቀንዳችሁን አታንሡ፤

5 ቀንዳችሁን እስከ ላይ አታንሡ፥ በእግዚአብሔርም ላይ ዓመፅን አትናገሩ።

6 ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረ በዳ የለምና፤

7 እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና ይህን ያዋርዳል ይህንም ያከብራል።

8 ጽዋ በእግዚአብሔር እጅ ነውና፤ ያልተቀላቀለ የወይን ጠጅ ሞላበት፤ ከዚህ ወደዚያ አገላበጠው፥ ነገር ግን አተላው አልፈሰሰም፤ የምድር ኃጢአተኞች ሁሉ ይጠጡታል።

9 እኔ ግን ለዘላለም ደስ ይለኛል፥ ለያዕቆብም አምላክ ዝማሬን አቀርባለሁ።

10 የኅጥኣንን ቀንዶች ሁሉ እሰብራለሁ፤ የጻድቃን ቀንዶች ግን ከፍ ከፍ ይላሉ።


መዝሙር 76

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ ስለ አሦራውያን፤ የአሳፍ የምስጋና መዝሙር።

1 እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ፥ ስሙም በእስራኤል ታላቅ ነው።

2 ስፍራው በሳሌም፥ ማደሪያውም በጽዮን ነው።

3 በዚያም የቀስትን ኃይል፥ ጋሻን ሰይፍን ሰልፍንም ሰበረ፤ በዚያም ቀንዶችን ሰበረ።

4 አንተ በዘላለም ተራሮች ሆነህ በድንቅ ታበራለህ።

5 ልበ ሰነፎች ሁሉ ደነገጡ፥ እንቅልፋቸውንም አንቀላፉ፤ ባለጠጎች ሁሉ በእነርሱ እጅ ምንም አላገኙም።

6 የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥ ከተግሣጽህ የተነሣ ፈረሰኞች ሁሉ አንቀላፉ።

7 አንተ ግን፥ አንተ ግሩም ነህ፤ ቍጣህን ማን ይቃወማል?

8 ፍርድን ከሰማይ አሰማህ፤ ምድር ፈራች ዝምም አለች፥

9 ልበ የዋሃን ያድን ዘንድ እግዚአብሔር ለፍርድ በተነሣ ጊዜ።

10 ሰው በፈቃዱ ያመሰግንሃልና፥ ከሕሊናቸው ትርፍም በዓልህን ያደርጋሉ።

11 ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ስእለትን ክፈሉ፤ በዙሪያው ያሉ ሁሉ እጅ መንሻን ለሚያስፈራው ያገባሉ።

12 የመኳንንትን ነፍስ ያወጣል፤ በምድርም ነገሥታት ዘንድ ያስፈራል።


መዝሙር 77

ለመዘምራን አለቃ፤ ስለ ኤዶታም፤ የአሳፍ መዝሙር።

1 በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ቃሌም ወደ እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም አደመጠኝ።

2 በመከራዬ ቀን እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እጆቼ በሌሊት በፊቱ ናቸው፥ አላረፍሁምም፥ ነፍሴም መጽናናትን አልቻለችም።

3 እግዚአብሔርን አሰብሁት ደስ አለኝም፤ ተናገርሁ፥ ነፍሴም ፈዘዘች።

4 ዓይኖቼ እንዲተጉ ያዝሃቸው፤ ደነገጥሁ አልተናገርሁም።

5 የዱሮውን ዘመን አሰብሁ፤ የዘላለሙን ዓመታት አሰብሁ፤ አጠናጠንሁም

6 በሌሊት ከልቤ ጋር ተጫወትሁ፥ ነፍሴንም አነቃቃኋት።

7 እግዚአብሔር ለዘላለም ይጥላልን? እንግዲህስ ቸርነቱን አይጨምርምን?

8 ለዘላለምስ ምሕረቱ ለልጅ ልጅ ተቈረጠችን? የተናገረውስ ቃል አልቆአልን?

9 እግዚአብሔርስ ሞገሱን ረሳን? በቍጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን?

10 ይህ ድካሜ ነው አልሁ፥ የልዑል ቀኝ እንደ ተለወጠ።

11 የእግዚአብሔርን ሥራ አስታወስሁ፤ የቀደመውን ተአምራትህን አስታወሳለሁና፤

12 በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፥ በሥራህም እጫወታለሁ።

13 አቤቱ፥ መንገድህ በመቅደስ ውስጥ ነው፤ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው?

14 ተኣምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ። ለሕዝብህ ኃይልን አስታወቅሃቸው።

15 የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች፥ ሕዝብህን በክንድህ አዳንሃቸው።

16 አቤቱ፥ ውኆች አዩህ፥ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፤ ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውኆችም ጮኹ።

17 ደመኖች ድምፅን ሰጡ፥ ፍላጾችህም ወጡ።

18 የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበረ፤ መብረቆች ለዓለም አበሩ፤ ምድር ተናወጠች ተንቀጠቀጠችም።

19 መንገድህ በባህር ውስጥ ነው፥ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፥ አረማመድህም አልታወቀም።

20 በሙሴና በአሮን እጅ ሕዝብህን እንደ በጎች መራሃቸው።


መዝሙር 78

የአሳፍ ትምህርት።

1 ሕዝቤ ሆይ፥ ሕጌን አድምጡ፤ ጆሮአችሁንም ወደ አፌ ቃል አዘንብሉ።

2 አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ፥ ያለውንም ተምሳሊት እናገራለሁ።

3 የሰማነውንና ያውቅነውን፥ አባቶቻችንም የነገሩንን፥ ለሚመጣ ትውልድ ከልጆቻቸው አልሰወሩም።

4 የእግዚአብሔርን ምስጋናና ኃይሉን ያደረገውንም ተኣምራት ተናገሩ።

5 ለልጆቻቸው ያስታውቅ ዘንድ ለአባቶቻችን ያዘዘውን ምስክር በያዕቆብ አቆመ፥ በእስራኤልም ሕግን ሠራ፤

6 የሚመጣ፥ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ፥ ተነሥተው ለልጆቻቸው ይነግራሉ፤

7 ተስፋቸውን በእግዚአብሔር እንዲያደርጉ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እንዳይረሱ፥ ትእዛዙንም እንዲጠብቁ፤

8 እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ ጠማማና የምታስመርር ትውልድ፥ ልብዋን ያላቀናች ትውልድ፥ ነፍስዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነች።

9 የኤፍሬም ልጆች ለሰልፍ ታጥቀው ቀስትንም ገትረው በሰልፍ ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ።

10 የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፥ በሕጉም ለመመላለስ እንቢ አሉ፤

11 መልካም ሥራውንና ያሳያቸውን ተኣምራቱን ረሱ፥

12 በግብጽ አገርና በጣኔዎስ በረሃ በአባቶቻቸው ፊት የሠራውን ተኣምራት።

13 ባሕርን ከፍሎ አሳለፋቸው፤ ውኆችን እንደ ክምር አቆመ።

14 ቀን በደመና መራቸው፥ ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን።

15 ዓለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤ ከጥልቅ እንደሚገኝ ያህል በብዙ አጠጣቸው።

16 ውኃን ከጭንጫ አወጣ፥ ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ።

17 ነገር ግን ይበድሉት ዘንድ እንደ ገና ደገሙ፥ ልዑልንም በምድረ በዳ አስቈጡት።

18 ለነፍሳቸው መብልን ይፈልጉ ዘንድ፥ እግዚአብሔርን በልባቸው ፈተኑት።

19 እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው አሙት። እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ ይችላልን?

20 ዓለቱን መታ፤ ውኆችም ወጡ፥ ወንዞችም ጐረፉ፤ እንጀራን መስጠትስ ይችላልን? ለሕዝቡስ ማዕድን ያዘጋጃልን?

21 እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፤ በያዕቆብም ላይ እሳት ነደደ፥ መዓትም በእስራኤል ላይ መጣ፤

22 በእግዚአብሔር አላመኑምና፥ በመድኃኒቱም አልተማመኑምና።

23 ደመናውንም ከላይ አዘዘ፥ የሰማይንም ደጆች ከፈተ፤

24 ይበሉም ዘንድ መናን አዘነበላቸው፥ የሰማይንም እንጀራ ሰጣቸው።

25 የመላክትንም እንጀራ ሰው በላ ስንቅንም እስኪተርፋቸው ላከላቸው።

26 ከሰማይ የምሥራቅን ነፋስ አስነሣ፥ በኃይሉም የደቡብን ነፋስ አመጣ፤

27 ሥጋን እንደ አፈር፥ የሚበርሩትንም ወፎች እንደ ባሕር አሸዋ አዘነበላቸው፤

28 በሰፈራቸው መካከል፥ በድንኳናቸውም ዙሪያ ወደቀ።

29 በሉ እጅግም ጠገቡ፤ ምኞታቸውንም ሰጣቸው።

30 ከወደዱትም አላሳጣቸውም፤ መብላቸውም ገና በአፋቸው ሳለ፥

31 የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው መጣ፥ ከእነርሱም ከፍ ያሉትን ገደለ፥ የእስራኤልንም ምርጦች አሰናከለ።

32 ከዚህም ሁሉ ጋር እንደ ገና በደሉ፥ ተኣምራቱንም አላመኑም፤

33 ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ፥ ዓመቶቻቸውም በችኰላ።

34 በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት፤ ተመለሱ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ፤

35 ረዳታቸውም እግዚአብሔር፥ መድኃኒታቸውም ልዑል አምላክ እንደ ሆነ አሰቡ።

36 በአፋቸው ብቻ ወደዱት፤ በአንደበታቸውም ዋሹበት፤

v37 ልባቸውም ከእርሱ ጋር አልቀናም፥ በቃል ኪዳኑም አልተማመኑትም።

38 እርሱ ግን መሓሪ ነው፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም፤ ቍጣውንም መመለስ አበዛ፥ መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም።

39 ወጥቶ የማይመለስ መንፈስ፥ ሥጋም እንደ ሆኑ አሰበ።

40 በምድረ በዳ ምን ያህል አስቈጡት፥ በበረሃም አሳዘኑት።

41 ተመለሱ፥ እግዚአብሔርንም ፈተኑት፥ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት።

42 እነርሱም እጁን አላሰቡም፥ ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀን፥

43 በግብጽ ያደረገውን ተኣምራቱን፥ በጣኔዎስም በረሃ ያደረገውን ድንቁን።

44 ወንዞቻቸውንም ወደ ደም ለወጠ፥ ምንጮቻቸውን ደግሞ እንዳይጠጡ።

45 ዝንቦችንም በላያቸው ሰደደባቸው፥ በሉአቸውም፤ በጓጉንቸርም አጠፋቸው።

46 ፍሬያቸውን ለኩብኩባ፥ ሥራቸውንም ለአንበጣ ሰጠ።

47 ወይናቸውን በበረዶ፥ በለሳቸውንም በአመዳይ አጠፋ።

48 እንስሶቻቸውን ለበረዶ፥ ሀብታቸውንም ለእሳት ሰጠ።

49 የመዓቱን መቅሠፍት በላያቸው ሰደደ፤ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ።

50 ለቍጣው መንገድን ጠረገ፤ ነፍሳቸውንም ከሞት አላዳናትም፥ እንስሶቻቸውንም በሞት ውስጥ ዘጋ፤

51 በኵሮቻቸውን ሁሉ በግብጽ፥ የድካማቸውንም መጀመሪያ በካም ድንኳኖች ገደለ።

52 ሕዝቡን ግን እንደ በጎች አሰማራቸው፥ እንደ መንጋም በምድረ በዳ መራቸው።

53 በተስፋም መራቸው አልፈሩምም፥ ጠላቶቻቸውንም ባሕር ደፈናቸው።

54 ወደ መቅደሱም ተራራ አገባቸው፥ ቀኙ ወደ ፈጠረችው ወደዚህች ተራራ፤

55 ከፊታቸውም አሕዛብን አባረረ፥ ርስቱንም በገመድ አካፈላቸው፥ የእስራኤልንም ወገኖች በቤታቸው አኖረ።

56 ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔርን ፈተኑት አስቈጡትም፥ ምስክሩንም አልጠበቁም፤

57 ተመለሱም እንደ አባቶቻቸውም ከዱ፤ እንደ ጠማማ ቀስትም ተገለበጡ፤

58 በኰረብታ መስገጃዎቻቸውም አስቈጡት፥ በተቀረጹ ምስሎቻቸውም አስቀኑት።

59 እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፥ እስራኤልንም እጅግ ናቀ፤

60 የሴሎምን ማደሪያ ተዋት በሰዎች መካከል ያደረገባትን ድንኳኑን፤

61 ኃይላቸውን ለምርኮ፥ ሽልማቱንም በጠላት እጅ ሰጠ።

62 ሕዝቡንም በጦር ውስጥ ዘጋቸው፥ ርስቱንም ቸል አላቸው።

63 ጕልማሶቻቸውን እሳት በላቸው፥ ቈነጃጅቶቻቸውም አላዘኑም፤

64 ካህናቶቻቸውም በሰይፍ ወደቁ፥ ባልቴቶቻቸውም አላለቀሱላቸውም።

65 እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፤

66 ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤ የዘላለምን ኀሣር ሰጣቸው።

67 የዮሴፍንም ድንኳን ተዋት፥ የኤፍሬምንም ወገን አልመረጠውም፤

68 የይሁዳን ወገን ግን መረጠ፥ የወደደውን የጽዮንን ተራራ።

69 መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፥ ለዘላለምም በምድር ውስጥ መሠረታት።

70 ዳዊትንም ባሪያውን መረጠው፥ ከበጎቹም መንጋ ውስጥ ወሰደው፤

71 ከሚያጠቡ በጎችም በኋላ፥ ባሪያውን ያዕቆብን ርስቱንም እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ወሰደው።

72 በልቡ ቅንነት ጠበቃቸው፥ በእጁም ብልሃት መራቸው።


መዝሙር 79

የአሳፍ መዝሙር።

1 አቤቱ፥ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ፤ የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ፥ ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት።

2 የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች መብል አደረጉ፥ የጻድቃንህንም ሥራ ለምድር አራዊት፤

3 ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውኃ አፈሰሱ፥ የሚቀብራቸውም አጡ።

4 ለጎረቤቶቻችንም ስድብ ሆንን፥ በዙሪያችንም ላሉ ሣቅና ዘበት።

5 አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘላለም ትቈጣለህ? ቅንዓትህም እንደ እሳት ይነድዳል?

6 ስምህን በማይጠሩ መንግሥታት ላይ በማያውቁህም አሕዛብ ላይ መዓትህን አፍስስ፤

7 ያዕቆብን በልተውታልና፥ ስፍራውንም ባድማ አድርገዋልና።

8 የቀደመውን በደላችንን አታስብብን፥ ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን፥ እጅግ ተቸግረናልና።

9 አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፥ እርዳን፤ ስለ ስምህ ክብር፥ አቤቱ፥ ታደገን፥ ስለ ስምህም ኃጢአታችንን አስተሰርይልን።

10 አሕዛብ፥ አምላካቸው ወዴት ነው? እንዳይሉ፥ የፈሰሰውን የባሪያዎችህን ደም በቀል በዓይኖቻችን ፊት አሕዛብ ያወቁ፤

11 የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ፤ እንደ ክንድህም ታላቅነት ሊገደሉ የተፈረደባቸውን አድን።

12 አቤቱ፥ የተዘባበቱብህን መዘባበታቸውን ለጎረቤቶቻችን ሰባት እጥፍ በብብታቸው ክፈላቸው።

13 እኛ ሕዝብህ ግን፥ የማሰማርያህም በጎች፥ ለዘላለም እናመሰግንሃለን፤ ለልጅ ልጅም ምስጋናህን እንናገራለን።


መዝሙር 80

ለመዘምራን አለቃ፤ በመለከቶች፤ ስለ አሦራውያን፤ የአሳፍ የምስክር መዝሙር።

1 ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ተገለጥ።

2 በኤፍሬምና በብንያም በምናሴም፤ ኃይልህን አንሣ እኛንም ለማዳን ና።

3 አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን።

4 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ በባሪያህ ጸሎት ላይ እስከ መቼ ትቈጣለህ?

5 የእንባ እንጀራን ትመግበናለህ፥ እንባም በስፍር ታጠጣናለህ።

6 ለጎረቤቶቻችን ክርክር አደረግኸን፥ ጠላቶቻችንም በላያችን ተሣለቁብን።

7 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን።

8 ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ፤ አሕዛብን አባረርህ እርስዋንም ተከልህ።

9 በፊትዋም ስፍራን አዘጋጀህ፥ ሥሮችዋንም ተከልህ ምድርንም ሞላች።

10 ጥላዋ ተራሮችን ከደነ፥ ጫፎችዋም እንደ እግዚአብሔር ዝግባ ሆኑ።

11 ቅርንጫፎችዋንም እስከ ባሕር፥ ቡቃያዋንም እስከ ወንዙ ዘረጋች።

12 አጥርዋን ለምን አፈረስህ? መንገድ አላፊም ሁሉ ይቀጥፋታል።

13 የዱር እርያ አረከሳት፥ የአገር አውሬም ተሰማራባት።

14 የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ እንግዲህ ተመለስ፤ ከሰማይ ተመልከት፥ እይም፥ ይህችንም የወይን ግንድ ጐብኝ።

15 በሰው ልጅ ለአንተ ያጸናኸውን ቀኝህ የተከላትን አንሣ።

16 በእሳት ተቃጥላለች ተነቅላማለች፤ ከፊትህ ተግሣጽም የተነሣ ይጠፋሉ።

17 ለአንተ ባጸናኸው በሰው ልጅ ላይ፥ በቀኝህ ሰው ላይ እጅህ ትሁን።

18 ከአንተም አንራቅ፤ አድነን ስምህንም እንጠራለን።

19 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን።


መዝሙር 81

ለመዘምራን አለቃ፤ በዋሽንት፤ የአሳፍ መዝሙር።

1 በረድኤታችን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፥ ለያዕቆብም አምላክ እልል በሉ።

2 ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር፤

3 በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፤

4 ለእስራኤል ሥርዓቱ ነውና፥ የያዕቆብም አምላክ ፍርድ።

5 ከግብጽ በወጣ ጊዜ ለዮሴፍ ምስክር አቆመው። ያላወቅሁትን ቋንቋ ሰማሁ።

6 ጫንቃውን ከሸክም፥ እጆቹንም በቅርጫት ከመገዛት አራቅሁ።

7 በመከራህ ጊዜ ጠራኸኝ አዳንሁህም፥ በተሰወረ ዐውሎም መለስሁልህ፥ በክርክር ውኃ ዘንድም ፈተንሁህ።

8 ሕዝቤ ሆይ፥ስማኝ እነግርሃለሁም፤ እስራኤል ሆይ፥ እመሰክርልሃለሁ።

9 አንተስ ብትሰማኝ ሌላ አምላክ አይሆንልህም፥ ለሌላ አምላክም አትሰግድም።

10 ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና፤ አፍህን አስፋ እሞላዋለሁም።

11 ሕዝቤ ግን ቃሌን አልሰሙኝም፥ እስራኤልም አላዳመጠኝም።

12 እንደ ልባቸው ሥራ ተውኋቸው፥ በልባቸውም አሳብ ሄዱ።

13 ሕዝቤስ ሰምቶኝ ቢሆን፥ እስራኤልም በመንገዴ ሄደው ቢሆን፤

14 ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባዋረድኋቸው ነበር፥ በሚያስጨንቋቸውም ላይ እጄን በጣልሁ ነበር፤

15 የእግዚአብሔር ጠላቶችም በተገዙለት ነበር፥ ዘመናቸውም ለዘላለም በሆነ ነበር፤

16 ከስንዴም ስብ ባበላቸው ነበር፥ ከዓለቱም ማር ባጠገባቸው ነበር።


መዝሙር 82

የአሳፍ መዝሙር።

1 እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ፥ በአማልክትም መካከል ይፈርዳል።

2 እስከ መቼ ሐሰትን ትፈርዳላችሁ? እስከ መቼ ለኃጢአተኞች ፊት ታደላላችሁ?

3 ለድሆችና ለድሀ አደጎች ፍረዱ፤ ለችግረኛውና ለምስኪኑ ጽድቅ አድርጉ፤

4 ብቸኛውንና ችግረኛውን አድኑ፤ ከኃጢአተኞችም እጅ አስጥሉአቸው።

5 አያውቁም፥ አያስተውሉም፤ በጨለማ ውስጥ ይመላለሳሉ፤ የምድር መሠረቶች ሁሉ ተናወጡ።

6 እኔ ግን። አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤

7 ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ፥ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ አልሁ።

8 አቤቱ፥ ተነሥ፥ በምድር ላይ ፍርድ፥ አንተ አሕዛብን ሁሉ ትወርሳለህና።


መዝሙር 83

የአሳፍ የምስጋና መዝሙር።

1 አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? አቤቱ፥ ዝም አትበል፥ ቸልም አትበል።

2 እነሆ፥ ጠላቶችህ ጮኽዋልና፥ የሚጠሉህም ራሳቸውን አንሥተዋልና።

3 ሕዝብህን በምክር ሸነገሉአቸው፥ በቅዱሳንህም ላይ ተማከሩ።

4 ኑ ከሕዝብ እናጥፋቸው፥ ደግሞም የእስራኤል ስም አይታሰብ አሉ።

5 አንድ ሆነው በአንተ ላይ ተማከሩ፤ በአንተ ላይ ቃል ኪዳን አደረጉ፤

6 የኤዶማውያን ድንኳኖች እስማኤላውያንም፥ ሞዓብም አጋራውያንም፥

7 ጌባል አሞንም አማሌቅም፥ ፍልስጥኤማውያንም ከጢሮስ ሰዎች ጋር፤

8 አሦርም ከእነርሱ ጋር ተባበረ፥ ለሎጥ ልጆችም ረዳት ሆኑአቸው።

9 እንደ ምድያምና እንደ ሲሣራ፥ በቂሶንም ወንዝ እንደ ኢያቢስ አድርግባቸው።

10 በዓይንዶር ጠፉ፥ እንደ ምድርም ጕድፍ ሆኑ።

11 አለቆቻቸውን እንደ ሔሬብና እንደ ዜብ፥ ታላላቆቻቸውንም እንደ ዛብሄልና እንደ ስልማና አድርጋቸው።

12 የእግዚአብሔርን መሠዊያ እንወርሳለን የሚሉትን።

13 አምላኬ ሆይ፥ እንደ ትቢያ በነፋስ ፊትም እንደ ገለባ አድርጋቸው።

14 እሳት ዱርን እንደሚያቃጥል፥ ነበልባልም ተራሮች እንደሚያነድድ፥

15 እንዲሁ በቍጣህ አሳድዳቸው፥ በመቅሠፍትህም አስደንግጣቸው።

16 ፊታቸውን እፍረት ሙላው፥ አቤቱ፥ ስምህንም ይፈልጋሉ።

17 ይፈሩ ለዘላለሙም ይታወኩ፤ ይጐስቍሉ ይጥፉም።

18 ስምህም እግዚአብሔር እንደ ሆነ፥ በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል እንደ ሆንህ ይወቁ።


መዝሙር 84

ለመዘምራን አለቃ፤ በዋሽንት፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር።

1 የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ ማደሪያዎችህ እንደምን የተወደዱ ናቸው!

2 ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትወድዳለች ትናፍቅማለች፤ ልቤም ሥጋዬም በሕያው አምላክ ደስ ተሰኘ።

3 ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች፥ ዋኖስም ጫጩቶችዋን የምታኖርበት ቤት አገኘች፤ የሠራዊት አምላክ ንጉሤም አምላኬም ሆይ፥ እርሱ መሠዊያህ ነው።

4 በቤትህ የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፤ ለዓለምና ለዘላለምም ያመሰግኑሃል።

5 አቤቱ፥ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት፥ በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው።

6 በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ በወሰነው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና።

7 ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል።

8 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፤ የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥ አድምጥ።

9 አቤቱ፥ መታመናችንን እይልን፥ ወደ ቀባኸውም ፊት ተመልከት።

10 ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ።

11 እግዚአብሔር አምላክ ምሕረትንና እውነትን ስለ ወደደ፥ ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም።

12 የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን ነው።


መዝሙር 85

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ለምድርህ ሞገስን አደረግህ፥ የያዕቆብንም ምርኮ መለስህ።

2 የሕዝብህን ኃጢአት አስቀረህ፥ አበሳቸውንም ሁሉ ከደንህ።

3 መዓትህንም ሁሉ አስወገድህ፤ ከቍጣህ መቅሠፍት ተመለስህ።

4 የመድኃኒታችን አምላክ ሆይ፥ መልሰን፥ ቍጣህንም ከእኛ መልስ።

5 በውኑ ለዘላለም ትቈጣናለህን? ቍጣህንስ ለልጅ ልጅ ታስረዝማለህን?

6 አቤቱ፥ ትመለሳለህ ታድነንማለህ፤ ሕዝቡም በአንተ ደስ ይላቸዋል።

7 አቤቱ፥ ምሕረትህን አሳየን፥ አቤቱ፥ መድኃኒትህንም ስጠን።

8 እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ፤ ሰላምን ለሕዝቡና ለቅዱሳኑ ልባቸውንም ወደ እርሱ ለሚመልሱ ይናገራልና።

9 ነገር ግን ክብር በምድራችን ያድር ዘንድ ማዳኑ ለሚፈሩት ቅርብ ነው፤

10 ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ።

11 እውነት ከምድር በቀለች፥ ጽድቅም ከሰማይ ተመለከተች።

12 እግዚአብሔርም በጎ ነገርን ይሰጣል፥ ምድራችንም ፍሬዋን ትሰጣለች።

13 ጽድቅ በፊቱ ይሄዳል፥ ፍለጋውንም በመንገድ ውስጥ ያኖራል።


መዝሙር 86

የዳዊት ጸሎት።

1 አቤቱ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም፥ ችግረኛና ምስኪን ነኝና።

2 ቅዱስ ነኝና ነፍሴን ጠብቅ፤ አምላኬ ሆይ፥ አንተን የታመነውን ባሪያህን አድነው።

3 አቤቱ፥ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና ማረኝ።

4 የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና።

5 አቤቱ፥ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህና፥ ምሕረትህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና።

6 አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ የልመናዬንም ድምፅ ስማ።

7 ትመልስልኛለህና በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጠራለሁ።

8 አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፥ እንደ ሥራህም ያለ የለም።

9 ያደረግሃቸው አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፥ አቤቱ፥ በፊትህም ይሰግዳሉ፥ ስምህንም ያከብራሉ፤

10 አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና።

11 አቤቱ፥ መንገድህን ምራኝ፥ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል።

12 አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ፤

13 ምሕረትህ በእኔ ላይ ታላቅ ናትና፥ ነፍሴንም ከታችኛይቱ ሲኦል አድነሃታልና።

14 አቤቱ፥ ዓመፀኞች በእኔ ላይ ተነሥተዋል፥ የክፉዎችንም ማኅበር ነፍሴን ፈለጉአት፤ በፊታቸውም አላደረጉህም።

15 አቤቱ፥ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ፤ መዓትህ የራቀ ምሕረትህም እውነትህም የበዛ፤

16 ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም፤ ለባሪያህ ኃይልህን ስጥ፥ የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን።

17 ምልክትንም ለመልካም ከእኔ ጋር አድርግ፤ የሚጠሉኝ ይዩ ይፈሩም፥ አቤቱ፥ አንተ ረድተኸኛልና፥ አጽንተኸኛልምና።


መዝሙር 87

የቆሬ ልጆች የምስጋና መዝሙር።

1 መሠረቶቹ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው፤

2 ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ፥ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል።

3 የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ፥ በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል።

4 የሚያውቁኝን ረዓብንና ባቢሎንን አስባቸዋለሁ፤ እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን ጢሮስም የኢትዮጵያም ሕዝብ፥ እነዚህ በዚያ ተወለዱ።

5 ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ፤ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።

6 እግዚአብሔር ለሕዝቡ፥ በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል።

7 በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ እንደሚላቸው ይነግራቸዋል።


መዝሙር 88

የቆሬ ልጆች የምስጋና መዝሙር። ለመዘምራን አለቃ በማኸላት ለመዘመር፤ የይዝራኤላዊው የኤማን ትምህርት።

1 አቤቱ፥ የመድኃኒቴ አምላክ፥ በቀንና በሌሊት በፊትህ ጮኽሁ፤

2 ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትግባ፥ ጆሮህንም ወደ ጩኸቴ አዘንብል፤

3 ነፍሴ መከራን ጠግባለችና፥ ሕይወቴም ወደ ሲኦል ቀርባለችና።

4 ወደ ጓድጓድ ከሚወርዱ ጋር ተቈጠርሁ፥ ረዳትም እንደሌለው ሰው ሆንሁ።

5 ለዘላለም እንደማታስባቸው፥ እንደ ተገደሉና በመቃብር ውስጥ እንደ ተጣሉ፥ በሙታን ውስጥ እንዳሉ የተጣልሁ ሆንሁ፤ እነርሱም ከእጅህ ተለዩ።

6 በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ፥ በታችኛው ጕድጓድ አስቀመጥኸኝ።

7 በእኔ ላይ ቍጣህ ጸና፥ መቅሠፍትህን ሁሉ በእኔ ላይ አመጣህ።

8 የሚያውቁኝን ከእኔ አራቅህ፤ በእነርሱ ዘንድ ርኵስ አደረግኸኝ፤ ያዙኝ፥ መውጫም የለኝም።

9 ዓይኖቼም በመከራ ፈዘዙ፤ አቤቱ፥ ሁልጊዜ ወደ አንተ ጮኽሁ፥ እጆቼንም ወደ አንተ ዘረጋሁ፥

10 በውኑ ለሙታን ተኣምራት ታደርጋለህን? የሞቱትስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን?

11 በመቃብርስ ውስጥ ቸርነትህን፥ እውነትህንስ በጥፋት ስፍራ ይናገራሉን?

12 ተአምራትህ በጨለማ፥ ጽድቅህንም በመርሳት ምድር ትታወቃለችን?

13 አቤቱ፥ እኔ ግን ወደ አንተ ጮኽሁ፤ በጥዋት ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትደርሳለች።

14 አቤቱ፥ ነፍሴን ለምን ትጥላለህ? ፊትህንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለህ?

15 እኔ ከታናሽነቴ ችግረኛ ለሞትም የቀረብሁ ነኝ፤ ከፍ ከፍ ካልሁ በኋላ ግን ተዋረድሁ ተናቅሁም።

16 መቅሠፍትህ በላዬ አለፈ፥ ግርማህም አስደነገጠኝ።

17 ሁልጊዜ እንደ ውኃ ከበቡኝ፥ በአንድነትም ያዙኝ።

18 ወዳጄንና ባልንጀራዬን ዘመዶቼንም ከመከራ የተነሣ ከእኔ አራቅህ።


መዝሙር 89

የይዝራኤላዊው የኤታን ትምህርት።

1 አቤቱ፥ ምሕረትህን ለዘላለም እዘምራለሁ፥ እውነትህንም በአፌ ለልጅ ልጅ እናገራለሁ።

2 እንዲህ ብለሃልና። ምሕረት ለዘላለም ይመሠረታል፥ እውነትህም በሰማይ ይጸናል።

3 ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ፥ ለባሪያዬም ለዳዊት ማልሁ።

4 ዘርህን ለዘላለም አዘጋጃለሁ፥ ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለሁ።

5 አቤቱ፥ ሰማያት ተኣምራትህን እውነትህንም ደግሞ በቅዱሳን ማኅበር ያመሰግናሉ።

6 እግዚአብሔርን በሰማይ የሚተካከለው ማን ነው? ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል?

7 በቅዱሳን ምክር እግዚአብሔር ክቡር ነው፤ በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው።

8 አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? አቤቱ፥ አንተ ብርቱ ነህ፥ እውነትህም ይከብብሃል።

9 የባሕርን ኃይል አንተ ትገዛለህ፥ የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ።

10 አንተ ረዓብን እንደ ተገደለ አዋረድኸው፥ በኃይልህም ክንድ ጠላቶችህን በተንሃቸው።

11 ሰማያት የአንተ ናቸው፥ ምድርም የአንተ ናት፤ ዓለምንና ሞላውም አንተ መሠረትህ።

12 ሰሜንና ደቡብን አንተ ፈጠርህ፤ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል።

13 ክንድህ ከኃይልህ ጋር ነው፤ እጅህ በረታች ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች።

14 የዙፋንህ መሠረት ጽድቅና ፍርድ ነው፤ ምሕረትና እውነት በፊትህ ይሄዳሉ።

15 እልልታ የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፤ አቤቱ፥ በፊትህ ብርሃን ይሄዳሉ።

16 በስምህ ቀኑን ሁሉ ደስ ይላቸዋል፥ በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ፤

17 የኃይላቸው ትምክሕት አንተ ነህና፥ በሞገስህም ቀንዳችን ከፍ ከፍ ይላልና።

18 ረድኤታችን ከእግዚአብሔር ከንጉሣችንም ከእስራኤል ቅዱስ ነውና።

19 በዚያ ጊዜ ለልጆችህ በራእይ ተናገርህ እንዲህም አልህ። ረድኤቴን በኃይል ላይ አኖርሁ፤ ከሕዝቤ የተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግሁ።

20 ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት።

21 እጄም ትረዳዋለች፥ ክንዴም ታጸናዋለች።

22 ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም፥ የዓመፃ ልጅም መከራ አይጨምርበትም።

23 ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ፥ የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ።

24 እውነቴና ምሕረቴም ከእርሱ ጋር ነው፥ በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል።

25 እጁን በባሕር ላይ ቀኙንም በወንዞች ላይ አኖራለሁ።

26 እርሱ። አባቴ አንተ ነህ፥ አምላኬ የመድኃኒቴም መጠጊያ ይላል።

27 እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፥ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል።

28 ለዘላለምም ምሕረቴን ለእርሱ እጠብቃለሁ፥ ኪዳኔም በእርሱ ዘንድ የታመነ ነው።

29 ዘሩንም ለዓለምና ለዘላለም፥ ዙፋኑንም እንደ ሰማይ ዘመን አደርጋለሁ።

30 ልጆቹ ግን ሕጌን ቢተዉ፥ በፍርዴም ባይሄዱ፤

31 ሥርዓቴንም ቢያረክሱ፥ ትእዛዜንም ባይጠብቁ፤

32 ኃጢአታቸውን በበትር፥ በደላቸውንም በመቅሠፍት እጐበኛታለሁ።

33 ምሕረቴን ግን ከእርሱ አላርቅም፥ በእውነቴም አልበድልም፤

34 ኪዳኔንም አላረክስም፥ ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም።

35 ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ።

36 ዘሩ ለዘላለም፥ ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሐይ ይኖራል።

37 ለዘላለም እንደ ጨረቃ ይጸናል፤ ምስክርነቱ በሰማይ የታመን ነው።

38 አንተ ግን ናቅኸው ጣልኸውም፥ የቀባኸውንም ጣልኸው።

39 የባሪያህንም ኪዳን አፈረስህ፥ መቅደሱንም በምድር አረከስህ።

40 ቅጥሩን ሁሉ ጣልህ፥ አምባዎቹንም አጠፋህ።

41 መንገድ አላፊም ሁሉ ተናጠቀው፥ ለጎረቤቶቹም ስድብ ሆነ።

42 የጠላቶቹንም ቀኝ ከፍ ከፍ አደረግህ፥ ጠላቶቹንም ሁሉ ደስ አሰኘህ።

43 የሰይፉንም ረድኤት መለስህ፥ በሰልፍም ውስጥ አልደገፍኸውም።

44 ከንጽሕናውም ሻርኸው፥ ዙፋኑንም በምድር ጣልህ።

45 የዙፋኑንም ዘመን አሳነስህ፥ በእፍረትም ሸፈንኸው።

46 አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘላለም ፊትህን ትመልሳለህ? እስከ መቼስ ቍጣህ እንደ እሳት ይነድዳል?

47 ችሎታዬ ምን እንደ ሆነ አስብ፤ በውኑ የሰውን ልጅ ሁሉ ለከንቱ ፈጠርኸውን?

48 ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ማን ነው? ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድን ማን ነው?

49 ለዳዊት በእውነት የማልህ፥ አቤቱ፥ የቀድሞ ምሕረትህ ወዴት ነው?

50 አቤቱ፥ የባሪያዎችህን ስድብ፥ በብብቴ ብዙ አሕዛብን የተቀበልሁትን፥

51 አቤቱ፥ ጠላቶችህን የሰደቡትን የቀባኸውን ዘመን የሰደቡትን አስብ።

52 እግዚአብሔር ለዘላለም ይባረክ። ይሁን ይሁን።


መዝሙር 90

የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎት።

1 አቤቱ፥ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን።

2 ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ።

3 ሰውን ወደ ኅሳር አትመልስም፤ የሰው ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ ትላለህ፤

4 ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ትጋት ነውና።

5 ዘመኖች የተናቁ ይሆናሉ፥ በማለዳም እንደ ሣር ያልፋል።

6 ማልዶ ያብባል ያልፋልም፥ በሠርክም ጠውልጎና ደርቆ ይወድቃል።

7 እኛ በቍጣህ አልቀናልና፥ በመዓትህም ደንግጠናልና።

8 የተሰወረውን ኃጢአታችንን በፊትህ ብርሃን፥ በደላችንንም በፊትህ አስቀመጥህ።

9 ዘመናችን ሁሉ አልፎአልና፥ እኛም በመዓትህ አልቀናልና፤ ዘመኖቻችንም እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ።

10 የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፥ እኛም እንገሠጻለንና።

11 የቍጣህን ጽናት ማን ያውቃል? ከቍጣህ ግርማ የተነሣ አለቁ።

12 በልብ ጥበብን እንድንማር፥ ቀኝህን እንዲህ አስታውቀን።

13 አቤቱ፥ ተመለስ፥ እስከ መቼስ ነው? ስለ ባሪያዎችህም ተምዋገት።

14 በማለዳ ምሕረትህን እንጠግባለን፤ በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን።

15 መከራ ባሳየኸን ዘመን ፈንታ፥ ክፉም ባየንባቸው ዘመኖች ፋንታ ደስ ይለናል።

16 ባሪያዎችህንና ሥራህን እይ፥ ልጆቻቸውንም ምራ።

17 የአምላካችን የእግዚአብሔር ብርሃን በላያችን ይሁን። የእጆቻችንንም ሥራ በላያችን አቅና።


መዝሙር 91

የዳዊት የምስጋና መዝሙር።

1 በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።

2 እግዚአብሔርን። አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ።

3 እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና።

4 በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል።

5 ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥

6 በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም።

7 በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም።

8 በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ብድራት ታያለህ።

9 አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፤ ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ።

10 ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም።

11 በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤

12 እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል።

13 በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ።

14 በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ።

15 ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ አከብረውማለሁ።

16 ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።


መዝሙር 92

በሰንበት ቀን የምስጋና መዝሙር።

1 እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ፤

2 በማለዳ ምሕረትን፥ በሌሊትም እውነትህን ማውራት

3 አሥር አውታር ባለው በበገና፥ ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ።

4 አቤቱ፥ በሥራህ ደስ አሰኝተኸኛልና፤ በእጅህም ሥራ ደስ ይለኛልና።

5 አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ትልቅ ነው፥ አሳብህም እጅግ ጥልቅ ነው።

6 ሰነፍ ሰው አያውቅም። ልብ የሌለውም ይህን አያስተውለውም።

7 ኃጢአተኞች እንደ ሣር ሲበቅሉ ዓመፃ የሚያደርጉ ሁሉ ሲለመልሙ፥ ለዘላለም ዓለም እንዲጠፋ ነው።

8 አቤቱ፥ አንተ ግን ለዘላለም ልዑል ነህ፤

9 አቤቱ፥ እነሆ፥ ጠላቶችህ ይጠፋሉና፥ ዓመፃንም የሚሠሩ ሁሉ ይበተናሉና።

10 ቀንዴ አንድ ቀንድ እንዳለው ከፍ ከፍ ይላል፤ ሽምግልናዬም በዘይት ይለመልማል።

11 ዓይኔም በጠላቶቼ ላይ አየች፥ ጆሮዬም በእኔ ላይ በቆሙ በክፉዎች ላይ ሰማች።

12 ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል።

13 በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ።

14 ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ።

15 አምላኬ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ ይነግራሉ፥ በእርሱም ዘንድ ዓመፃ የለም።


መዝሙር 93

በሰንበት ቀን የምስጋና መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ነገሠ፥ ክብርንም ለበሰ፤ እግዚአብሔር ኃይልን ለበሰ፥ ታጠቀም፤ ዓለምን እንዳትናወጥ አጸናት።

2 ዙፋንህ ከጥንት ጀምሮ የተዘጋጀ ነው፥ አንተም ከዘላለም ነህ።

3 አቤቱ፥ ወንዞች ከፍ ከፍ አደረጉ፥ ወንዞች ቃሎቻቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ።

4 ከብዙ ውኆች ድምፅ ከባሕርም ታላቅ ሞገድ ይልቅ እግዚአብሔር በከፍታው ድንቅ ነው።

5 ምስክርህ እጅግ የታመነ ነው፤ አቤቱ፥ እስከ ረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ቅድስና ይገባል።


መዝሙር 94

በአራተኛ ሰንበት የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው። የበቀል አምላክ ተገለጠ።

2 የምድር ፈራጅ ሆይ፥ ከፍ ከፍ በል፤ ለትዕቢተኞች ፍዳቸውን ክፈላቸው።

3 አቤቱ፥ ኃጢአተኞች እስከ መቼ? ኃጢአተኞች እስከ መቼ ይጓደዳሉ?

4 ይከራከራሉ፥ ዓመፃንም ይናገራሉ፤ ዓመፃንም የሚያደርጉ ሁሉ ይናገራሉ።

5 አቤቱ፥ ሕዝብን አዋረዱ፥ ርስትህንም አስቸገሩ።

6 ባልቴቲቱንና ድሀ አደጉን ገደሉ፥ ስደተኛውንም ገደሉ።

7 እግዚአብሔር አያይም፥ የያዕቆብ አምላክ አያስተውልም አሉ።

8 የሕዝብ ደንቆሮች ሆይ፥ አስተውሉ፤ ሰነፎችማ መቼ ይጠበባሉ?

9 ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን?

10 አሕዛብንስ የሚገሥጸው፥ ለሰውም እውቀት የሚያስተምረው እርሱ አይዘልፍምን?

11 የሰዎች አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ያውቃል።

12-13 ለኃጢአተኛ ጕድጓድ እስኪቈፈር ድረስ ከክፉዎች ዘመናት ይወገድ ዘንድ፥ አቤቱ፥ አንተ የገሠጽኸው ሕግህንም ያስተማርኸው ሰው ምስጉን ነው።

14 እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፥ ርስቱንም አይተውምና

15 ፍርድ ወደ ጽድቅ እስኪመልስ ድረስ ልበ ቅኖችም ሁሉ ይከተሉአታል።

16 በክፉዎች ላይ ለእኔ የሚቆም ማን ነው? ዓመፃንስ በሚያደርጉ ላይ ለእኔ የሚከራከር ማን ነው?

17 እግዚአብሔር የረዳኝ ባይሆን ነፍሴ ለጥቂት ጊዜ በሲኦል ባደረች ነበር።

18 እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ፥ አቤቱ፥ ምሕረትህ ረዳኝ።

19 አቤቱ፥ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።

20 በሕግ ላይ ዓመፅን የሚሠራ የዓመፅ ዙፋን ከአንተ ጋር አንድ ይሆናልን?

21 የጻድቅን ነፍስ ያደቡባታል፥ በንጹሕ ደምም ይፈርዳሉ።

22 እግዚአብሔር መጠጊያ ሆነኝ፥ አምላኬ የተስፋዬም ረዳት ነው።

23 እንደ በደላቸውም እንደ ክፋታቸውም ፍዳቸውን ይከፍላቸዋል፥ አምላካችን እግዚአብሔርም ያጠፋቸዋል።


መዝሙር 95

የዳዊት ምስጋና መዝሙር።

1 ኑ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን፤ ለአምላክ ለመድኃኒታችን እልል እንበል።

2 በምስጋና ወደ ፊቱ እንድረስ፥ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል፤

3 እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ ታላቅ ንጉሥ ነውና።

4 እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥላቸውም፤ የምድር ዳርቻዎችም በእጁ ውስጥ ናቸው፥ የተራሮች ከፍታዎች የእርሱ ናቸው።

5 ባሕር የእርሱ ናት እርሱም አደረጋት፥ የብስንም እጆቹ ሠሩአት።

6 ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤

7 እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና።

8 በምድረ በዳ እንደ ተፈታተኑት እንዳስቈጡት ጊዜ፥ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ።

9 የተፈታተኑኝ አባቶቻችሁ ፈተኑኝ ሥራዬንም አዩ።

10 ያችን ትውልድ አርባ ዓመት ተቈጥቻት ነበር። ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፥ እነርሱም መንገዴን አላወቁም አልሁ።

11 ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቁጣዬ ማልሁ።


መዝሙር 96

ከምርኮ በኋላ ቤት በተሠራ ጊዜ።

1 ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፤ ምድር ሁሉ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ።

2 እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ባርኩ፥ ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ።

3 ክብሩን ለአሕዛብ ተኣምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ፤

4 እግዚአብሔር ታላቅ ምስጋናውም ብዙ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነውና።

5 የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።

6 ምስጋናና ውበት በፊቱ፥ ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው።

7 የአሕዛብ ወገኖች፥ ለእግዚአብሔር አምጡ፥ ክብርና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ፤

8 ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ቍርባን ያዙ ወደ አደባባዮችም ግቡ።

9 በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ፤ ምድር ሁሉ በፊቱ ትነዋወጥ።

10 በአሕዛብ መካከል። እግዚአብሔር ነገሠ በሉ። እንዳይናወጥም ዓለሙን እርሱ አጸናው፥ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል።

11 ሰማያት ደስ ይበላቸው፥ ምድርም ሐሤትን ታድርግ፤ ባሕርና ሞላዋ ይናወጡ፤

12 በረሃ በእርስዋም ያሉ ሁሉ ሐሤትን ያድርጉ፤ የዱር ዛፎች ሁሉ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል፤

13 ይመጣልና፤ በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና፤ እርሱም ዓለምን በጽድቅ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል።


መዝሙር 97

1 እግዚአብሔር ነገሠ፤ ምድር ሐሤትን ታድርግ፥ ብዙ ደሴቶችም ደስ ይበላቸው።

2 ደመና ጭጋግም በዙሪያው ናቸው፤ ጽድቅና ፍርድ የዙፋኑ መሠረት ናቸው።

3 እሳት በፊቱ ይሄዳል፥ ጠላቶቹንም በዙሪያው ያቃጥላል።

4 መብረቆቹ ለዓለም አበሩ፤ ምድር አየችና ተናወጠች።

5 ተራሮችም ከእግዚአብሔር ፊት፥ ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት እንደ ሰም ቀለጡ።

6 ሰማያት የእርሱን ጽድቅ አወሩ፥ አሕዛብም ሁሉ ክብሩን አዩ።

7 ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ፥ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ፤ መላእክቱ ሁሉ፥ ስገዱለት።

8 አቤቱ፥ ስለ ፍርድህ ጽዮን ሰምታ ደስ አላት፥ የይሁዳም ሴት ልጆች ደስ አላቸው፤

9 አንተ፥ እግዚአብሔር፥ በምድር ላይ ሁሉ ልዑል ነህና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ እጅግ ከፍ ከፍ ብለሃልና።

10 እግዚአብሔርን የምትወዱ፥ ክፋትን ጥሉ፤ እግዚአብሔር የቅዱሳኑን ነፍሶች ይጠብቃል፥ ከኃጥኣንም እጅ ያድናቸዋል።

11 ብርሃን ለጻድቃን፥ ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ።

12 ጻድቃን፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፥ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ።


መዝሙር 98

የዳዊት መዝሙር።

1 ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፥ እግዚአብሔር ተኣምራትን አድርጎአልና፤ ቀኙ የተቀደሰም ክንዱ ለእርሱ ማዳን አደረገ።

2 እግዚአብሔር ማዳኑን አስታወቀ፥ በአሕዛብም ፊት ጽድቁን ገለጠ።

3 ለያዕቆብ ምሕረቱን ለእስራኤልም ቤት እውነቱን አሰበ፤ የምድር ዳርቻዎች ሁሉ የአምላካችንን ማዳን አዩ።

4 ምድር ሁሉ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ አመስግኑ፥ ደስ ይበላችሁ፥ ዘምሩም።

5 ለእግዚአብሔር በመሰንቆ፥ በመሰንቆና በዝማሬ ድምፅ ዘምሩ።

6 በዋሽንትና በመለከት ድምፅ በንጉሥ በእግዚአብሔር ፊት እልል በሉ።

7 ባሕርና ሞላዋ፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ይናወጡ።

8 ወንዞችም በአንድነት በእጅ ያጨብጭቡ፤ ተራሮች ደስ ይበላቸው፥ በምድር ሊፈርድ ይመጣልና።

9 ለዓለምም በጽድቅ ለአሕዛብም በቅንነት ይፈርዳል።


መዝሙር 99

የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ነገሠ፥ አሕዛብ ይደንግጡ፤ በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ፥ ምድር ትናወጥ።

2 እግዚአብሔር በጽዮን ታላቅ ነው፤ እርሱም በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ አለ።

3 ግሩምና ቅዱስ ነውና ሁሉ ታላቅ ስምህን ያመስግኑ።

4 የንጉሥ ክብር ፍርድን ይወድዳል፤ አንተ ቅንነትን አጸናህ፥ ለያዕቆብ ፍርድንና ጽድቅን አንተ አደረግህ።

5 አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ ቅዱስ ነውና ወደ እግሩ መረገጫ ስገዱ።

6 ሙሴና አሮን በካህናቱ ዘንድ፥ ሳሙኤልም ስሙን በሚጠሩት ዘንድ ናቸው። እግዚአብሔርን ጠሩት፥ እርሱም መለሰላቸው።

7 በደመና ዓምድም ተናገራቸው፤ ምስክሩንና የሰጣቸውን ትእዛዝ ጠበቁ።

8 አቤቱ አምላክችን ሆይ፥ አንተ ሰማሃቸው፤ አቤቱ፥ አንተ ማርሃቸው፥ ሥራቸውን ሁሉ ግን ተበቀልሃቸው።

9 አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ በቅዱስ ተራራውም ስገዱ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና።


መዝሙር 100

የምስጋና መዝሙር።

1 ምድር ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፥

2 በደስታም ለእግዚአብሔር ተገዙ፥ በሐሤትም ወደ ፊቱ ግቡ።

3 እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም፤ እኛስ ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን።

4 ወደ ደጆቹ በመገዛት፥ ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤ አመስግኑት፥ ስሙንም ባርኩ፤

5 እግዚአብሔር ቸር፥ ምሕረቱም ለዘላለም፥ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነውና።