መዝሙር 101

የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ምሕረትንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ።

2 እዘምራለሁ፥ ንጹሕ መንገዱንም አስተውላለሁ፤ ወደ እኔ መቼ ትመጣለህ? በቤቴ መካከል በልቤ ቅንነት እሄዳለሁ።

3 በዓይኔ ፊት ክፉን ነገር አላኖርሁም፤ ሕግ ተላላፊዎችን ጠላሁ።

4 ጠማማ ልብም አልተጠጋኝም፤ ክፉ ከእኔ በራቀ ጊዜ አላወቅሁም።

5 ባልንጀራውን በቀስታ የሚያማን እርሱን አሳደድሁ፤ በዓይኑ ትዕቢተኛ የሆነውና ልቡ የሚሳሳው ከእኔ ጋር አይተባበርም።

6 ከእኔ ጋር ይኖሩ ዘንድ፤ ዓይኖቼ በምድር ምእመናን ላይ ናቸው፤ በቀና መንገድ የሚሄድ እርሱ ያገለግለኛል።

7 ትዕቢትን የሚያደርግ በቤቴ መካከል አይኖርም፤ ዓመፅን የሚናገር በዓይኔ ፊት አይቀናም።

8 ዓመፃ የሚያደርጉትን ሁሉ ከእግዚአብሔር ከተማ አጠፋቸው ዘንድ፥ የምድርን ኃጢአተኞች ሁሉ በማለዳ እገድላቸዋለሁ።


መዝሙር 102

ባዘነና ልመናውን በእግዚአብሔር ፊት ባፈሰሰ ጊዜ የችግረኛ ጸሎት።

1 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ ጩኸቴም ወደ አንተ ይድረስ።

2 በመከራዬ ቀን ፊትህን ከኔ አትመልስ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ በጠራሁህ ቀን ፈጥነህ ስማኝ።

3 ዘመኔ እንደ ጢስ አልቃለችና፥ አጥንቶቼም እንደ መቃጠያ ተቃጥለዋልና።

4 እህል መብላት ተረስቶኛልና ተቀሠፍሁ ልቤም እንደ ሣር ደረቀ።

5 ከጩኸቴ ድምፅ የተነሣ አጥንቶቼ ከሥጋዬ ጋር ተጣበቁ።

6 እንደ ምድረ በዳ እርኩም መሰልሁ፤ በፈረሰ ቤት እንዳለ እንደ ጕጕት ሆንሁ።

7 ተጋሁ፥ በሰገነትም እንደሚኖር ብቸኛ ድንቢጥ ሆንሁ።

8 ጠላቶቼ ሁልጊዜ ይሰድቡኛል፥ የሚያሳድዱኝም ተማማሉብኝ።

9 አመድን እንደ እህል ቅሜአለሁና፥ መጠጤንም ከእንባዬ ጋር ቀላቅያለሁና፥

10 ከቍጣህና ከመዓትህም የተነሣ፤ አንሥተኸኛልና፥ ጥለኸኝማልና።

11 ዘመኖቼ እንደ ጥላ አዘንብለዋል፤ እኔም እንደ ሣር ደርቄአለሁ።

12 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ለዘላለም ትኖራለህ፥ መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው።

13 አንተ ተነሥ ጽዮንንም ይቅር በላት፥ የምሕረትዋ ጊዜ ነውና፥ ዘመንዋም ደርሶአልና፤

14 ባሪያዎችህም ድንጋዮችዋን ወድደዋልና፥ ለመሬትዋም አዝነዋልና።

15 አቤቱ፥ አሕዛብ ስምህን፥ ነገሥታትም ሁሉ ክብርህን ይፈራሉ፤

16 እግዚአብሔር ጽዮንን ይሠራታልና፥ በክብሩም ይገለጣልና።

17 ወደ ችግረኞች ጸሎት ተመለከተ፥ ልመናቸውንም አልናቀም።

18 ይህ ለሚመጣ ትውልድ ይጻፍ፥ የሚፈጠርም ሕዝብ ለእግዚአብሔር እልል ይላል፤

19 እግዚአብሔር ከመቅደሱ ከፍታ ሆኖ ተመልክቶአልና፥ ከሰማይ ሆኖ ምድርን አይቶአልና፤

20 የእስረኞችን ጩኸት ይሰማ ዘንድ፥ ሊገድሉ የተፈረደባቸውን ያድን ዘንድ፤

21 የእግዚአብሔርን ስም በጽዮን ምስጋናውንም በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ፤

22 አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ መንግሥታትም ለእግዚአብሔር ይገዙ ዘንድ።

23 በኃይሉ ጎዳና መለሰለት። የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ።

24 በዘመኔ እኵሌታ አትውሰደኝ፤ ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው።

25 አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው።

26 እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤

27 አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።

28 የባሪያዎችህም ልጆች ይኖራሉ፥ ዘራቸውም ለዘላለም ትጸናለች።


መዝሙር 103

የዳዊት መዝሙር።

1 ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ አጥንቶቼም ሁሉ፥ የተቀደሰ ስሙን።

2 ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ ምስጋናውንም ሁሉ አትርሺ፤

3 ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፥

4 ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት፥ በምሕረቱና በቸርነቱ የሚከልልሽ፥

5 ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፥ ጕልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል።

6 እግዚአብሔር ይቅርታ አድራጊ ነው፤ ለተበደሉ ሁሉ ይፈርዳል።

7 ለሙሴ መንገዱን አስታወቀ፥ ለእስራኤል ልጆችም አደራረጉን።

8 እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፥ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ።

9 ሁልጊዜም አይቀሥፍም፥ ለዘላለምም አይቈጣም።

10 እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም።

11 ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ።

12 ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ።

13 አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤

14 ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ።

15 ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፤

16 ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና፥ ስፍራውንም ደግሞ አያውቀውምና።

17 የእግዚአብሔር ምሕረት ግን ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ፥ ጽድቁም በልጅ ልጆች ላይ ነው፤

18 ቃል ኪዳኑን በሚጠብቁ፥ ትእዛዙንም ያደርጉአት ዘንድ በሚያስቡ ላይ ነው።

19 እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አዘጋጀ፥ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች።

20 ቃሉን የምትፈጽሙ፥ ብርቱዎችና ኃያላን፥ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ።

21 ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ።

22 ፍጥረቶቹ ሁሉ በግዛቱ ስፍራ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ። ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ።


መዝሙር 104

የዳዊት መዝሙር።

1 ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፤ ክብርንና ግርማን ለበስህ።

2 ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስህ፤ ሰማይንም እንደ መጋረጃ ዘረጋህ፤

3 እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሰረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥

4 መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል።

5 ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት።

6 በጥልቅ እንደ ልብስ ከደንሃት፥ በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ።

7 ከዘለፋህም ይሸሻሉ፥ ከነጐድጓድህም ድምፅ ይደነግጣሉ፤

8 ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥ ወደ ቈላዎች ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ ይወርዳሉ፤

9 እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው ምድርን ይከድኑ ዘንድ እንዳይመለሱ።

10 ምንጮችን ወደ ቈላዎች ይልካል፤ በተራሮች መካከል ውኆች ያልፋሉ፤

11 የዱር አራዊትን ሁሉ ያጠጣሉ፥ የበረሃ አህያዎችም ጥማታቸውን ይረካሉ።

12 የሰማይም ወፎች በእነርሱ ዘንድ ያድራሉ፥ በድንጋዩ ስንጥቅ መካከልም ይጮኻሉ።

13 ተራሮችን ከላይ የሚያጠጣቸው፤ ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች።

14 እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ ለምለሙን ለሰው ልጆች ጥቅም፥ ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል።

15 ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል፥ እህልም የሰውን ጕልበት ያጠነክራል።

16 የእግዚአብሔር ዛፎች እርሱም የተከላቸው የሊባኖስ ዝግባዎች ይጠግባሉ።

17 በዚያም ወፎች ይዋለዳሉ፥ የሽመላ ቤትም የእነርሱ ጎረቤት ነው።

18 ረጃጅም ተራራዎች ለዋላዎች፥ ድንጋዮችም ለእሽኮኮች መሸሻ ናቸው።

19 ጨረቃን ለጊዜዎች አደረገ፤ ፀሐይም መግቢያውን ያውቃል።

20 ጨለማ ታደርጋለህ ሌሊትም ይሆናል፤ በእርሱም የዱር አራዊት ሁሉ ይወጡበታል።

21 የአንበሳ ግልገሎች ለመንጠቅ ይጮኻሉ፥ ከእግዚአብሔርም ምግባቸውን ይሻሉ።

22 ፀሐይ ስትወጣ ይሰበሰባሉ በየዋሻቸውም ይተኛሉ።

23 ሰው ወደ ተግባሩ፥ እስኪመሽም ድረስ ወደ ሥራው ይወጣል።

24 አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፥ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች።

25 ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፤ በዚያ ስፍራ ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፥ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ።

26 በዚያ ጊዜ መርከቦች ይሄዳሉ፥ በዚያም ላይ የፈጠርኸው ዘንዶ ይጫወትበታል።

27 ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ።

28 በሰጠሃቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ፤ እጅህን ትከፍታለህ፥ ከመልካም ነገርም ይጠግባሉ።

29 ፊትህን ስትሰውር ይደነግጣሉ፤ ነፍሳቸውን ታወጣለህ ይሞታሉም፥ ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ።

30 መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥ የምድርንም ፊት ታድሳለህ።

31 የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ይሁን፤ እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይለዋል።

32 ምድርን ያያል እንድትንቀጠቀጥም ያደርጋል፤ ተራሮችን ይዳስሳል ይጤሳሉም።

33 በሕይወቴ ሳለሁ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፥ ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ሁሉ እዘምራለሁ።

34 ቃሌ ለእርሱ ይጣፍጠው፥ እኔም በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል።

35 ኅጥኣን ከምድር ይጥፉ፤ ዓመፀኞች እንግዲህ አይገኙ። ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ። ሃሌ ሉያ።


መዝሙር 105

ሃሌ ሉያ።

1 እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ፥ ለአሕዛብም ሥራውን አውሩ።

2 ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ።

3 በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው።

4 እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።

5-6 ባሪያዎቹ የአብርሃም ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ የሠራትን ድንቅ አስቡ፥ ተአምራቱን የአፉንም ፍርድ።

7 እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው።

8 ቃል ኪዳኑን ለዘላለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥

9 ለአብርሃም ያደረገውን፥ ለይስሐቅም የማለውን፤

10 ለያዕቆብ ሥርዓት እንዲሆን ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን እንዲሆን አጸና።

11 እንዲህም አለ። ለአንተ የከነዓንን ምድር የርስታችሁን ገመድ እሰጣለሁ፤

12 ይህም የሆነው እነርሱ በቍጥር ጥቂቶች ሰዎች፥ እጅግ ጥቂቶችና ስደተኞች ሲሆኑ ነው።

13 ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥ ከመንግሥታትም ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ።

14-15 የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ።

16 በምድር ላይ ራብን ጠራ፥ የእህልን ኃይል ሁሉ ሰበረ።

17 በፊታቸው ሰውን ላከ፤ ዮሴፍ ለባርነት ተሸጠ።

18 እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፥ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ።

19 ቃሉ እስኪመጣለት ድረስ፥ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው።

20 ንጉሥ ላከ ፈታውም፥ የአሕዛብም አለቃ አስፈታው።

21 የቤቱ ጌታ፥ የጥሪቱ ሁሉ ገዢ አደረገው፥

22 አለቆቹን እንደ ፈቃዱ ይገሥጽ ዘንድ፥ ሽማግሌዎቹንም ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ።

23 እስራኤልም ወደ ግብጽ ገባ፥ ያዕቆብም በካም አገር ተቀመጠ።

24 ሕዝቡንም እጅግ አበዛ፥ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው።

25 ሕዝቡን ይጠሉ ዘንድ በባሪያዎቹም ላይ ይተነኰሉ ዘንድ ልባቸውን ለወጠ።

26 ባሪያውን ሙሴን የመረጠውንም አሮንን ላከ።

27 የተኣምራቱን ነገር በላያቸው ድንቁንም በካም አገር አደረገ።

28 ጨለማን ላከ ጨለመባቸውም፤ በቃሉም ዐመፁ።

29 ውኃቸውን ወደ ደም ለወጠ፥ ዓሦቻቸውንም ገደለ።

30 ምድራቸው የንጉሦቻቸውም ቤቶች በጓጕንቸር ሞሉ።

31 ተናገረ፥ የውሻ ዝንብ ትንኝም በዳርቻቸው መጡ።

32 ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፥ እሳትም በምድራቸው ተቃጠለች።

33 ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፥ የአገራቸውንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ።

34 ተናገረ፥ አንበጣም ስፍር ቍጥር የሌለውም ኩብኩባ መጣ፥

35 የአገራቸውንም ለምለም ሁሉ በላ፥ የምድራቸውንም ፍሬ በላ።

36 የአገራቸውንም በኵር ሁሉ፥ የጕልበታቸውን መጀመሪያ ሁሉ መታ።

37 ከወርቅና ከብርም ጋር አወጣቸው፥ በወገናቸውም ውስጥ ደዌ አልነበረም።

38 ፈርተዋቸው ነበርና ግብጽ በመውጣታቸው ደስ አላት።

39 ደመናን ለመሸፈኛ ዘረጋባቸው፥ እሳትንም በሌሊት ያበራላቸው ዘንድ ዘረጋ።

40 ለመኑ፥ ድርጭትንም አመጣላቸው፥ የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው።

41 ዓለቱን ሰነጠቀ፥ ውኃውም ፈሰሰ፤ ወንዞች በበረሃ ሄዱ፤

42 ለባሪያው ለአብርሃም የነገረውን ቅዱስ ቃሉን አስቦአልና።

43 ሕዝቡንም በደስታ የተመረጡትንም በእልልታ አወጣ።

44 የአሕዛብንም አገሮች ሰጣቸው፥ የወገኖችንም ድካም ወረሱ፥

45 ሕጉን ይጠብቁ ዘንድ፥ ሥርዓቱንም ይፈልጉ ዘንድ። ሃሌ ሉያ


መዝሙር 106

1 ሃሌ ሉያ፤ ቸር ነውና፥ ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ።

2 የእግዚአብሔርን ኃይል ሥራ ማን ይናገራል? ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ያሰማል?

3 ፍርድን የሚጠብቁ፥ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ምስጉኖች ናቸው።

4 አቤቱ፥ በሕዝብህ ሞገስ አስበን፥ በመድኃኒትህም ጐብኘን፤

5 የመረጥሃቸውን በጎነት እናይ ዘንድ፥ በሕዝብህም ደስታ ደስ ይለን ዘንድ፥ ከርስትህም ጋር እንጓደድ ዘንድ።

6 ከአባቶቻችን ጋር ኃጢአትን ሠራን፥ ዐመፅንም፥ በደልንም።

7 አባቶቻችን በግብጽ ሳሉ ተኣምራትህን አላስተዋሉም፥ የምሕረትህንም ብዛት አላሰቡም፤ በኤርትራ ባሕር ባለፉ ጊዜ ዐመፁብህ።

8 ኃይሉን ግን ለማስታወቅ። ስለ ስሙ አዳናቸው።

9 የኤርትራንም ባሕር ገሠጸ እርሱም ደረቀ፤ እንደ ምድረ በዳ በጥልቅ መራቸው።

10 ከሚጠሉአቸውም እጅ አዳናቸው፥ ከጠላትም እጅ ተቤዣቸው።

11 ያሳደዱአቸውንም ውኃ ደፈናቸው፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም።

12 በዚያን ጊዜ በቃሉ አመኑ፥ ምስጋናውንም ዘመሩ።

13 ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልታገሡም።

14 በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት።

15 የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ።

16 ሙሴንም እግዚአብሔር የቀደሰውንም አሮንን በሰፈር ተመቀኙአቸው።

17 ምድርም ተከፈተች ዳታንንም ዋጠችው፥ የአቤሮንንም ወገን ደፈነች፤

18 በማኅበራቸውም እሳት ነደደች፥ ነበልባልም ኅጥኣንን አቃጠላቸው።

19 በኮሬብም ጥጃን ሠሩ፥ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ።

20 ሣርም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ።

21-22 ታላቅ ነገርንም በግብጽ፥ ድንቅንም በካራን ምድር፥ ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባሕር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ።

23 እንዳያጠፋቸው ቍጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ።

24 የተወደደችውን ምድር ናቁ፥ በቃሉም አልታመኑም፥

25 በድንኳኖቻቸውም ውስጥ አንጐራጐሩ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም።

26-27 በምድረ በዳም ይጥላቸው ዘንድ፥ ዘራቸውንም በአሕዛብ መካከል ይጥል ዘንድ፥ በየአገሩም ይበትናቸው ዘንድ፥ እጁን አነሣባቸው።

28 በብዔል ፌጎርም ተባበሩበት፥ የሙታንንም መሥዋዕት በሉ።

29 በሥራቸውም አስመረሩት፥ ቸነፈርም በላያቸው በዛ።

30 ፊንሐስም ተነሥቶ ፈረደባቸው፥ ቸነፈሩም ተወ፤

31 ያም እስከ ዘላለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።

32-33 በክርክር ውኃ ዘንድም አስቈጡት፥ መንፈሱን አስመርረዋታልና፤ ስለ እነርሱም ሙሴ ተበሳጨ፤ በከንፈሮቹም በስንፍና ተናገረ።

34 እግዚአብሔርም እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም፤

35 ከአሕዛብም ጋር ተደባለቁ፥ ሥራቸውንም ተማሩ።

36 ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ፥ ወጥመድም ሆኑባቸው።

37 ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠው፤

38 የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸን ደም፥ ለከነዓን ጣዖቶች የሠውአቸውን ንጹሕ ደም አፈሰሱ፥ ምድርም በደም ረከሰች።

39 በሥራቸው ረከሱ፥ በማድረጋቸውም አመነዘሩ።

40 የእግዚአብሔርም ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፥ ርስቱንም ተጸየፈ።

41 ወደ አሕዛብም እጅ አሳለፋቸው፥ የሚጠሉአቸውም ገዙአቸው።

42 ጠላቶቻቸውም ግፍ አደረጉባቸው፥ ከእጃቸውም በታች ተዋረዱ።

43 ብዙ ጊዜ አዳናቸው፤ ነገር ግን በምክራቸው አስመረሩት፥ በኃጢአታቸውም ተዋረዱ።

44 እርሱ ግን ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ ጭንቃቸውን ተመለከተ፤

45 ለእነርሱም ኪዳኑን አሰበ፥ እንደ ምሕረቱም ብዛት ተጸጸተ።

46 በማረኩአቸውም ሁሉ ፊት ሞገስን ሰጣቸው።

47 አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን።

48 ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ ሕዝብም ሁሉ አሜን ይበል። ሃሌ ሉያ።


መዝሙር 107

ሃሌ ሉያ።

1 ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤

2 እግዚአብሔር ያዳናቸው፥ ከጠላቶች እጅ ያዳናቸው ይናገሩ።

3 ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከባሕር፥ ከየአገሩ ሰበሰባቸው።

4 ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ፤ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም።

5 ተራቡ ተጠሙም፥ ነፍሳቸውም በውስጣቸው አለቀች።

6 በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው፤

7 ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ የቀና መንገድን መራቸው።

8 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤

9 የተራበችን ነፍስ አጥግቦአልና፥ የተራቈተችንም ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና።

10 በጨለማ በሞትም ጥላ የተቀመጡ፥ በችግር በብረትም የታሰሩ፤

11 የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ዐመፁ፥ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ፥

12 ልባቸው በድካም ተዋረደ፤ ታመሙ የሚረዳቸውም አጡ።

13 በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ በመከራቸውም አዳናቸው።

14 ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ እስራታቸውንም ሰበረ።

15 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤

16 የናሱን ደዶች ሰብሮአልና፥ የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጦአልና።

17 ስለ ዓመፃቸው ሰነፉ፥ ስለ ኃጢአታቸውም ተቸገሩ።

18 ሰውነታቸው መብልን ሁሉ ተጸየፈች፥ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ።

19 በተጨነቁ ጊዜም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው።

20 ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም፥ ከጥፋታቸውም አዳናቸው።

21 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመሰግኑ፤

22 የምስጋና መሥዋዕትንም ይሠውለት፥ በእልልታም ሥራውን ይንገሩ።

23 በመርከቦች ወደ ባሕር የሚወርዱ፥ በታላቅ ውኃ ሥራቸውን የሚሠሩ፥

24 እነርሱ የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በጥልቅም ያለችውን ድንቁን አዩ።

25 ተናገረ፥ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ፥ ሞገድም ከፍ ከፍ አለ።

26 ወደ ሰማይ ይወጣሉ ወደ ጥልቅም ይወርዳሉ፤ ነፍሳቸውም በመከራ ቀለጠች።

27 ደነገጡ እንደ ስካርም ተንገደገዱ፥ ጥበባቸውም ሁሉ ተዋጠች።

28 በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው።

29 ዐውሎንም ጸጥ አደረገ፥ ሞገዱም ዝም አለ።

30 ዝም ብሎአልና ደስ አላቸው፤ ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው።

31 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ።

32 በአሕዛብ ጉባኤ ከፍ ከፍ ያድርጉት፥ በሽማግሌዎችም ሸንጎ ያመስግኑት።

33 ወንዞችን ምድረ በዳ፥ የውኃውንም ምንጮች ደረቅ አደረጋቸው፤

34 ከተቀመጡባት ክፋት የተነሣ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት።

35 ምድረ በዳን ለውኃ መቆሚያ፥ ደረቁንም ምድር የውኃ ምንጮች አደረገ።

36 በዚያም ራብተኞችን አስቀመጠ፥ የሚኖርባትንም ከተማ ሠሩ።

37 እርሻዎችንም ዘሩ ወይኖችንም ተከሉ፥ የእህልንም ሰብል አደረጉ።

38 ባረካቸውም እጅግም በዙ፤ እንስሶቻቸውንም አላሳነሰባቸውም።

39 እነርሱ በችግር በክፋት በጭንቀት ተዋረዱ እያነሱም ሄዱ፤

40 በአለቶችም ላይ ኅሣርን፥ አፈሰሰ፥ መንገድም በሌለበት በምድረ በዳ አሳታቸው።

41 ችግረኛንም ከችግሩ ረዳው፤ እንደ በጎች መንጋ ወገን አደረገው።

42 ቅኖች ያያሉ፥ ደስም ይላቸዋል፤ ኃጢአትም ሁሉ አፍዋን ትዘጋለች።

43 ጥበበኛ የሆነና ይህን የሚጠብቅ ማን ነው? እርሱ የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።


መዝሙር 108

የዳዊት የምስጋና መዝሙር።

1 ልቤ ጽኑ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጽኑ ነው፤ እቀኛለሁ በክብሬም እዘምራለሁ።

2 በገና ሆይ፥ ተነሥ፥ መሰንቆም፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ።

3 አቤቱ፥ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፥ በወገኖችም መካከል እዘምርልሃለሁ፤

4 ምሕረትህ በሰማይ ላይ ታላቅ ናትና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ ነውና።

5 አቤቱ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፥ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።

6 ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ፤ በቀኝህ አድን አድምጠኝም።

7 እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ። ደስ ይለኛል፥ ሴኬምንም እካፈላለሁ፥ የሱኮትንም ሸለቆ እሰፍራለሁ።

8 ገለዓድ የእኔ ነው ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው። ይሁዳ ንጉሤ ነው።

9 ሞዓብ መታጠቢያዬ ነው፥ በኤዶምያስ ላይም ጫማዬን እዘረጋለሁ፤ ፍልስጥኤም ይገዙልኛል።

10 ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል?

11 አቤቱ፥ የጣልኸኝ አንተ አይደለህምን? አምላክ ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም።

12 በመከራችን ረድኤትን ስጠን፤ የሰውም ማዳን ከንቱ ነው።

13 በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን፤ እርሱም የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋል።


መዝሙር 109

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አምላክ ሆይ፥ ምሥጋናዬን ዝም አትበል፥

2 የኃጢአተኛ አፍና የተንኰለኛ አፍ በላዬ ተላቅቀውብኛልና፤ በሽንገላ አንደበትም በላዬ ተናገሩ፤

3 በጥል ቃል ከበቡኝ፥ በከንቱም ተሰለፉብኝ።

4 በወደድኋቸው ፋንታ አጣሉኝ፥ እኔ ግን እጸልያለሁ።

5 በመልካም ፋንታ ክፉን በወደድኋቸውም ፋንታ ጠላትነትን መለሱልኝ።

6 በላዩ ኃጢአተኛን ሹም፤ ሰይጣንም በቀኙ ይቁም።

7 በተምዋገተም ጊዜ ተረትቶ ይውጣ፤ ጸሎቱም ኃጢአት ትሁንበት።

8 ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ፤ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ።

9 ልጆቹም ድሀ አደግ ይሁኑ፥ ሚስቱም መበለት ትሁን።

10 ልጆቹም ተናውጠው ይቅበዝበዙ ይለምኑም፥ ከስፍራቸውም ይባረሩ።

11 ባለዕዳም ያለውን ሁሉ ይበርብረው፥ እንግዶችም ድካሙን ሁሉ ይበዝብዙት።

12 የሚያግዘውንም አያግኝ። ለድሀ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር።

13 ልጆቹ ይጥፉ፤ በአንድ ትውልድ ስሙ ይደምሰስ።

14 የአባቶቹ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ትታሰብ፤ የእናቱም ኃጢአት አትደምሰስ።

15 በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ይኑሩ፤ መታሰቢያቸው ከምድር ይጥፋ።

16 ምሕረትን ያደርግ ዘንድ አላሰበምና ችግረኛንና ምስኪንን ልቡ የተሰበረውንም ሰው ይገድል ዘንድ አሳደደ።

17 መርገምን ወደደ ወደ እርሱም መጣች፤ በረከትንም አልመረጠም ከእርሱም ራቀች።

18 መርገምን እንደ ልብስ ለበሳት፥ እንደ ውኃም ወደ አንጀቱ፥ እንደ ቅባትም ወደ አጥንቱ ገባች።

19 እንደሚለብሰው ልብስ። ሁልጊዜም እንደሚታጠቀው ትጥቅ ይሁነው።

20 ይህ ሥራ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚያጣሉኝ በነፍሴም ላይ ክፉን በሚናገሩ ነው።

21 አንተ ግን አቤቱ ጌታዬ፥ ስለ ስምህ ምሕረትህን በእኔ ላይ አድርግ፤ ምሕረትህ መልካም ናትና አድነኝ።

22 እኔ ችግረኛ ምስኪንም ነኝና፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ።

23 እንዳለፈ ጥላ አለቅሁ፥ እንደ አንበጣም እረገፍሁ።

24 ጕልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ።

25 እኔም በእነርሱ ዘንድ ለነውር ሆንሁ፤ ባዩኝ ጊዜ ራሳቸውን ነቀነቁ።

26 አቤቱ አምላኬ፥ እርዳኝ፥ እንደ ምሕረትህም አድነኝ።

27 አቤቱ፥ እጅህ ይህች እንደ ሆነች፥ አንተም ይህችን እንዳደረግህ ይወቁ።

28 እነርሱ ይራገማሉ አንተ ግን ባርክ፤ በእኔ ላይ የሚነሡ ይፈሩ፥ ባሪያህ ግን ደስ ይበለው።

29 የሚያጣሉኝ እፍረትን ይልበሱ፤ እፍረታቸውን እንደ መጐናጸፊያ ይልበሱአት።

30 እግዚአብሔርን በአፌ እጅግ አመሰግነዋለሁ። በብዙዎችም መካከል አከብረዋለሁ፤

31 ነፍሱን ከሚያሳድዱአት ያድን ዘንድ በድሀ ቀኝ ቆሞአልና።


መዝሙር 110

የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ጌታዬን። ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።

2 እግዚአብሔር የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፤ በጠላቶችህም መካከል ግዛ።

3 ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀን፥ በቅዱሳን ብርሃን፥ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ።

4 እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ፥ እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም።

5 እግዚአብሔር በቀኝህ ነገሥታትን በቍጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል።

6 በአሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ ሬሳዎችንም ያበዛል፤ በሰፊ ምድር ላይ ራሶችን ይቀጠቅጣል።

7 በመንገድ ከፈሳሽ ውኃ ይጠጣል፤ ስለዚህ ራስ ከፍ ከፍ ይላል።


መዝሙር 111

1 ሃሌ ሉያ። አቤቱ፥ በቅኖች ሸንጎ በጉባኤም በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ።

2 የእግዚአብሔር ሥራ ታላቅ ናት፥ ደስ በሚሰኙባት ሁሉ ዘንድ የተፈለገች ናት።

3 ሥራው ምስጋናና ግርማ ነው፤ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል።

4 ለተአምራቱ መታሰቢያን አደረገ፤ እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው።

5 ለሚፈሩት ምግብን ሰጣቸው፤ ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል።

6 የአሕዛብን ርስት ይሰጣቸው ዘንድ ለሕዝቡ የሥራውን ብርታት አሳየ።

7 የእጆቹ ሥራ እውነትና ፍርድ ነው፤ ትእዛዙም ሁሉ የታመነ ነው፥

8 ለዘላለምም የጸና ነው፥ በእውነትና በቅንም የተሠራ ነው።

9 መድኃኒትንም ለሕዝቡ ሰደደ፥ ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤ ስሙ የተቀደሰና የተፈራ ነው።

10 የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥ ለሚያደርጓትም ሁሉ ደኅና ማስተዋል አላቸው፤ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።


መዝሙር 112

1 ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድድ ሰው ምስጉን ነው።

2 ዘሩ በምድር ላይ ኃያል ይሆናል፤ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች።

3 ክብርና ባለጠግነት በቤቱ ነው፥ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል።

4 ለቅኖች ብርሃን በጨለማ ወጣ፤ መሓሪና ይቅር ባይ ጻድቅም ነው።

5 ቸር ሰው ይራራል ያበድራልም፥ በፍርድም ነገሩን ይፈጽማል።

6 ለዘላለም አይናወጥም፤ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል።

7 ከክፉ ነገር አይፈራም፤ በእግዚአብሔር ለመታመን ልቡ የጸና ነው።

8 በጠላቶቹ ላይ እስኪያይ ድረስ ልቡ ጽኑ ነው፥ አይፈራም።

9 በተነ ለችግረኞችም ሰጠ፤ ጽድቁ ለዘላለም ዓለም ይኖራል፤ ቀንዱ በክብር ከፍ ከፍ ይላል።

10 ኃጢአተኛም አይቶ ይቈጣል፥ ጥርሱንም ያፋጫል፥ ይቀልጣልም፤ የኃጢአተኞችም ምኞት ትጠፋለች።


መዝሙር 113

1 ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥ የእግዚአብሔርንም ስም አመስግኑ።

2 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን።

3 ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያው ድረስ የእግዚአብሔር ስም ይመስገን።

4 እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍተኛ ነው፥ ክብሩም ከሰማያት በላይ ነው።

5 እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ማን ነው? በላይ የሚኖር፤

6 በሰማይና በምድር የተዋረዱትን የሚያይ፤

7-8 ከአለቆች ጋር ከሕዝቡም አለቆች ጋር ያኖረው ዘንድ ችግረኛን ከመሬት የሚያነሣ፥ ምስኪኑንም ከፋንድያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ፤

9 መካኒቱን በቤት የሚያኖራት፥ ደስ የተሰኘችም የልጆች እናት የሚያደርጋት። ሃሌ ሉያ።


መዝሙር 114

ሃሌ ሉያ።

1 እስራኤል ከግብጽ፥ የያዕቆብም ቤት ከእንግዳ ሕዝብ በወጣ ጊዜ፥

2 ይሁዳ መቅደሱ፥ እስራኤልም ግዛቱ ሆነ።

3 ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ።

4 ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ።

5 አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ፥ምን ሆናችኋል?

6 እናንተም ተራሮች፥ እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችስ፥ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ?

7 ከያዕቆብ አምላክ ፊት፥ ከጌታ ፊት ምድር ተናወጠች፤

8 ድንጋዩን ወደ ውኃ መቆሚያ፥ ጭንጫውንም ወደ ውኃ ምንጭ ከለወጠ።


መዝሙር 115

1 ለእኛ አይደለም፥ አቤቱ፥ ለእኛ አይደለም፥ ነገር ግን ለስምህ ስለ ምሕረትህ ስለ እውነትህም ምስጋናን ስጥ።

2 አሕዛብ። አምላካቸው ወዴት ነው? አይበሉ።

3 አምላካችንስ በላይ በሰማይ ነው፤ በሰማይም በምድርም የፈቀደውን ሁሉ አደረገ።

4 የአሕዛብ ጣዖታቶች የወርቅና የብር፥ የሰው እጅ ሥራ ናቸው።

5 አፍ አላቸው አይናገሩምም፤ ዓይን አላቸው አያዩምም፤

6 ጆሮ አላቸው አይሰሙምም፤ አፍንጫ አላቸው አያሸትቱምም፤

7 እጅ አላቸው አይዳሰሱምም፤ እግር አላቸው አይሄዱምም፤ በጕሮሮአቸውም አይናገሩም።

8 የሚሠሩአቸውም የሚያምኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ።

9 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ ረድኤታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው።

10 የአሮን ቤት ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ ረድኤታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው።

11 እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ ረድኤታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው።

12 እግዚአብሔር አሰበን ይባርከንማል፤ የእስራኤልን ቤት ይባረካል፥ የአሮንንም ቤት ይባረካል።

13 እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ ትንንሾችንና ትልልቆችን ይባርካል።

14 እግዚአብሔር በላያችሁ፥ በላያችሁና በልጆቻችሁ ላይ ይጨምር።

15 እናንተ ሰማይንና ምድርን ለሠራ ለእግዚአብሔር የተባረካችሁ ናችሁ።

16 የሰማያት ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት።

17 አቤቱ፥ ሙታን የሚያመሰግኑህ አይደሉም ወደ ሲኦልም የሚወርዱ ሁሉ፤

18 እኛ ሕያዋን ግን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔርን እንባርካለን። ሃሌ ሉያ።


መዝሙር 116

ሃሌ ሉያ።

1 እግዚአብሔር የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና ወደድሁት።

2 ጆሮውን ወደ እኔ አዘንብሎአልና በዘመኔ ሁሉ እጠራዋለሁ።

3 የሞት ጣር ያዘኝ፥ የሲኦልም ሕማም አገኘኝ፤ ጭንቀትንና መከራን አገኘሁ።

4 የእግዚአብሔርንም ስም ጠራሁ። አቤቱ፥ ነፍሴን አድናት።

5 እግዚአብሔር መሓሪና ጻድቅ ነው፥ አምላካችንም ይቅር ባይ ነው።

6 እግዚአብሔር ሕፃናትን ይጠብቃል፤ ተቸገርሁ እርሱም አዳነኝ።

7 ነፍሴ ሆይ፥ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፥ እግዚአብሔር መልካም አድርጎልሻልና፤

8 ነፍሴን ከሞት፥ ዓይኔንም ከእንባ፥ እግሬንም ከመሰናከል አድኖአልና።

9 በሕያዋን አገር በእግዚአብሔር ፊት እሄዳለሁ።

10 አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ፤ እኔም እጅግ ተቸገርሁ።

11 እኔም ከድንጋጤዬ የተነሣ። ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ነው አልሁ።

12 ስላደረገልኝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምንን እመልሳለሁ?

13 የመድኃኒትን ጽዋ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ።

14 በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ።

15 የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።

16 አቤቱ፥ እኔ ባሪያህ ነኝ፥ ባሪያህ ነኝ፥ የሴት ባሪያህም ልጅ ነኝ፤ ሰንሰለቴን ሰበርህ።

17 ለአንተ የምስጋና መሥዋዕትን እሠዋለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ።

18 በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ፥

19 በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ፥ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ በመካከልሽም። ሃሌሉያ


መዝሙር 117

ሃሌ ሉያ።

1 አሕዛብ ሁላችሁ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑት፥ ወገኖችም ሁሉ ያመስግኑት፤

2 ምሕረቱ በእኛ ላይ ጸንታለችና፤ የእግዚአብሔርም እውነት ለዘላለም ትኖራለች። ሃሌ ሉያ።


መዝሙር 118

ሃሌ ሉያ።

1 እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና።

2 ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች የእስራኤል ቤት አሁን ይንገሩ።

3 ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች የአሮን ቤት አሁን ይንገሩ።

4 ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ አሁን ይንገሩ።

5 በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ ሰማኝ አሰፋልኝም።

6 እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል?

7 እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ እኔም በጠላቶቼ ላይ አያለሁ።

8 በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።

9 በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ ይሻላል።

10 አሕዛብ ሁሉ ከበቡኝ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው፤

11 መክበቡንስ ከበቡኝ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው፤

12 ንብ ማርን እንዲከብብ ከበቡኝ፥ እሳትም በእሾህ ውስጥ እንዲነድድ ነደዱ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው።

13 ገፋኸኝ፥ ለመውደቅም ተንገዳገድሁ፤ እግዚአብሔር ግን አገዘኝ።

14 ኃይሌም ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም መድኃኒት ሆነልኝ።

15 የእልልታና የመድኃኒት ድምፅ በጻድቃን ድንኳን ነው፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች።

16 የእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገችኝ፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች።

17 አልሞትም በሕይወት እኖራለሁ እንጂ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እናገራለሁ።

18 መገሠጽስ እግዚአብሔር ገሠጸኝ፤ ለሞት ግን አልሰጠኝም።

19 የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤ ወደ እነርሱ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።

20 ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤ ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ።

21 ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ።

22 ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፥

23 ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፥ ለዓይናችንም ድንቅ ናት።

24 እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።

25 አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና።

26 በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ።

27 እግዚአብሔር አምላክ ነው፥ ለእኛም በራልን፤ እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ የበዓሉን መሥዋዕት በገመድ እሰሩት።

28 አንተ አምላኬ ነህ አመሰግንህማለሁ። አንተ አምላኬ ነህ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ።

29 እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና።


መዝሙር 119

አሌፍ

1 በመንገዳቸው ንጹሐን የሆኑ፥ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው።

2 ምስክሩን የሚፈልጉ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው፤

3 ዓመፅንም አያደርጉም፥ በመንገዶቹም ይሄዳሉ።

4 ትእዛዛትህን እጅግ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝህ።

5 ሥርዓትህን ለመጠበቅ፤ መንገዶቼ ይቀኑ ዘንድ እወድድ ነበር።

6 ትእዛዝህን ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርም።

7 አቤቱ፥ የጽድቅህን ፍርድ ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ።

8 ሥርዓትህን እጠብቃለሁ፤ በፍጹም አትጣለኝ።

ቤት

9 ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው።

10 በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ።

11 አንተ እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።

12 አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዓትህን አስተምረኝ።

13 የአፍህን ፍርድ ሁሉ በከንፈሬ ነገርሁ።

14 እንደ ብልጥግና ሁሉ በምስክርህ መንገድ ደስ አለኝ።

15 ትእዛዝህን አሰላስላለሁ፥ መንገድህንም እፈልጋለሁ።

16 በትእዛዝህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም።

ጋሜል

17 ለባሪያህ መልካም አድርግ ሕያው እንድሆን፥ ቃልህንም እንድጠብቅ።

18 ዓይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ።

19 እኔ በምድር እንግዳ ነኝ፤ ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር።

20 ነፍሴ ሁልጊዜ ፍርድህን እጅግ ናፈቀች።

21 ከትእዛዛትህ የሳቱትን ትዕቢተኞችንና ርጉማንን ዘለፍህ።

22 ምስክርህን ፈልጌአለሁና። ስድብንና ነውርን ከእኔ አርቅ።

23 አለቆች ደግሞ ተቀምጠው እኔን አሙኝ፤ ባሪያህ ግን ሕግህን ያሰላስል ነበር።

24 ምስክርህም ተድላዬ ነው፥ ሥርዓትህም መካሪዬ ነው።

ዳሌጥ

25 ነፍሴ ወደ ምድር ተጠጋች፤ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ።

26 መንገድህን ነገርሁ ሰማኸኝም፤ ሥርዓትህን አስተምረኝ።

27 የሥርዓትህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ተኣምራትህንም አሰላስላለሁ።

28 ከኀዘን የተነሣ ነፍሴ አንቀላፋች፤ በቃልህ አጠንክረኝ።

29 የዓመፅን መንገድ ከእኔ አርቅ፥ በሕግህም ማረኝ፤

30 የእውነትህን መንገድ መረጥሁ፥ ፍርድህንም አልረሳሁም።

31 አቤቱ፥ ምስክርህን ተጠጋሁ፤ አታሳፍረኝ።

32 ልቤን ባሰፋኸው ጊዜ፥ በትእዛዝህ መንገድ ሮጥሁ።

33 አቤቱ፥ የሥርዓትህን መንገድ አስተምረኝ፥ ሁልጊዜም እፈልገዋለሁ።

34 እንዳስተውል አድርገኝ፥ ሕግህንም እፈልጋለሁ፤ በፍጹም ልቤም እጠብቀዋለሁ።

35 እርስዋን ወድጃለሁና የትእዛዝህን መንገድ ምራኝ።

36 ልቤን ወደ ምስክርህ አዘንብል፥ ወደ ስስትም አይሁን።

37 ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዓይኖቼን መልስ፤ በመንገድህ ሕያው አድርገኝ።

38 እንዲፈራህ ባሪያህን በቃልህ አጽና።

39 ፍርድህ መልካም ናትና የተጠራጠርሁትን ስድብ ከእኔ አርቅ።

40 እነሆ፥ ትእዛዝህን ናፈቅሁ፤ በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ

ዋው

41 አቤቱ፥ እንደ ቃልህ፥ ምሕረትህና መድኃኒትህ ይምጡልኝ።

42 በቃልህ ታምኛለሁና ለሚሰድቡኝ በነገር እመልስላቸዋለሁ።

43 በፍርድህም ታምኛለሁና የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ።

44 ለዘላለም ዓለም ሁልጊዜ ሕግህን እጠብቃለሁ።

45 ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና አስፍቼ እሄዳለሁ።

46 በነገሥታት ፊት ምስክርህን እናገራለሁ፥ አላፍርምም፤

47 እጅግም በወደድኋቸው በትእዛዛትህ ደስ ይለኛል።

48 እጆቼንም ወደ ወደድኋቸው ወደ ትእዛዛትህ አነሣለሁ፤ ሥርዓትህንም አሰላስላሁ።

ዛይ

49 ለባሪያህ ተስፋ ያስደረግኸውን ቃልህን አስብ።

50 ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና ይህች በመከራዬ ደስ አሰኘችኝ።

51 ትዕቢተኞች እጅግ ዐመፁ፤ እኔ ግን ከሕግህ አልራቅሁም።

52 ከጥንት የነበረውን ፍርድህን አሰብሁ፥ አቤቱ፥ ተጽናናሁም።

53 ሕግህን ከተዉ ከኃጢአተኞች የተነሣ ኅዘን ያዘኝ።

54 በእንግድነቴ አገር ሥርዓትህ መዝሙር ሆነችኝ።

55 አቤቱ፥ በሌሊት ስምህን አሰብሁ፥ ሕግህንም ጠበቅሁ።

56 ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና፤ ይህች ሆነችልኝ።

ሔት

57 እግዚአብሔር ክፍሌ ነው፤ ሕግህን እጠብቃለሁ አልሁ።

58 በፍጹም ልቤ ወደ ፊትህ ተማለልሁ፤ እንደ ቃልህ ማረኝ።

59 ስለ መንገዶችህ አሰብሁ፥ እግሬንም ወደ ምስክሮችህ መለስሁ።

60 ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ አልዘገየሁምም።

61 የኃጥኣን ገመዶች ተተበተቡብኝ፤ ሕግህን ግን አልረሳሁም።

62 ስለ ጽድቅህ ፍርድ፥ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ።

63 እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፥ ትእዛዝህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ።

64 አቤቱ፥ ምሕረትህ በምድር ሁሉ ሞላች፤ ሥርዓትህን አስተምረኝ።

ጤት

65 አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ለባሪያህ መልካም አደረግህ።

66 በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካም ምክርና እውቀትን አስተምረኝ።

67 እኔ ሳልጨነቅ ሳትሁ፤ አሁን ግን ቃልህን ጠበቅሁ።

68 አቤቱ፥ አንተ ቸር ነህ፥ በቸርነትህም ሥርዓትህን አስተምረኝ።

69 የትዕቢተኞች ዓመፅ በላዬ በዛ፤ እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዛትህን እፈልጋለሁ።

70 ልባቸው እንደ ወተት ረጋ፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል።

71 ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ።

72 ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል።

ዮድ

73 እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፤ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ።

74 በቃልህ ታምኛለሁና የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል።

75 አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥ በእውነትህም እንዳስቸገርኸኝ አወቅሁ።

76 ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባሪያህ ይሁነው።

77 ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር።

78 ትዕቢተኞች በዓመፅ ጠምመውብኛልና ይፈሩ፤ እኔ ግን በትእዛዝህ እጫወታለሁ።

79 የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ።

80 እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን።

ካፍ

81 ነፍሴ መድኃኒትህን ናፈቀች፤ በቃልህም ታመንሁ።

82 መቼ ታጽናናኛለህ እያልሁ ዓይኖቼ ስለ ቃልህ ፈዘዙ።

83 በጢስ እንዳለ አቁማዳ ሆኛለሁና፤ ሥርዓትህን ግን አልረሳሁም።

84 የባሪያህ ዘመኖች ስንት ናቸው? በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለህ?

85 ኃጢአተኞች ጨዋታን ነገሩኝ፥ አቤቱ፥ እንደ ሕግህ ግን አይደለም።

86 ትእዛዛትህ ሁሉ እውነት ናቸው፤ በዓመፅ አሳድደውኛል፤ እርዳኝ።

87 ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፤ እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም።

88 እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፤ የአፍህንም ምስክር እጠብቃለሁ።

ላሜድ

89 አቤቱ፥ ቃልህ በሰማይ ለዘላለም ይኖራል።

90 እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፤ ምድርን መሠረትሃት እርስዋም ትኖራለች።

91 ሁሉም ባሪያዎችህ ናቸውና ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል።

92 ሕግህ ተድላዬ ባይሆን፥ ቀድሞ በጐስቍልናዬ በጠፋሁ ነበር።

93 በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድህን ለዘላለም አልረሳም።

94 እኔ የአንተ ነኝ፤ ፍርድህን ፈልጌአልሁና አድነኝ።

95 ኃጢአተኞች ያጠፉኝ ዘንድ ጠበቁኝ፤ ምስክርህን ግን መረመርሁ።

96 የሥራህን ሁሉ ፍጻሜ አየሁ፤ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው።

ሜም

97 አቤቱ፥ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው።

98 ለዘላለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ።

99 ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ።

100 ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ።

101 ቃልህን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ።

102 አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም።

103 ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ።

104 ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ።

ኖን

105 ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።

106 የጽድቅህን ፍርድ እጠብቅ ዘንድ ማልሁ፥ አጸናሁም።

107 እጅግ ተቸገርሁ፤ አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ።

108 አቤቱ፥ ከአፌ የሚወጣውን ቃል ውደድ፥ ፍርድህንም አስተምረኝ።

109 ነፍሴ ሁልጊዜ በእጅህ ውስጥ ናት፤ ሕግህን ግን አልረሳሁም።

110 ኃጢአተኞች ወጥመድን ዘረጉብኝ፤ ከትእዛዝህ ግን አልሳትሁም።

111 የልቤ ደስታ ነውና ምስክርህን ለዘላለም ወረስሁ።

112 ለዘላለም ለፍጻሜውም ትእዛዝህን አደርግ ዘንድ ልቤን አዘነበልሁ።

ሳምኬት

113 ዓመፀኞችን ጠላሁ፥ ሕግህን ግን ወደድሁ።

114 አንተ ረዳቴና መጠጊያዬ ነህ፥ በቃልህም ተማመንሁ።

115 እናንተ ኃጢአተኞች፥ ከእኔ ራቁ፥ የአምላኬንም ትእዛዝ ልፈልግ።

116 እንደ ቃልህ ደግፈኝ፥ ሕያውም እሆናለሁ። ከተስፋዬም አልፈር።

117 እርዳኝ እድናለሁም፥ ሁልጊዜም ሥርዓትህን እመረምራለሁ።

118 ምኞታቸው ዓመፃ ነውና ከሥርዓትህ የሚርቁትን ሁሉ አጐሳቈልሃቸው።

119 የምድርን ኃጢአተኞች ሁሉ እንደ ርኵሰት አጠፋሃቸው፤ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ።

120 ሥጋዬ አንተን ከመፍራት የተነሣ ደንገጠ፤ ከፍርድህ የተነሣ ፈርቻለሁ።

121 ፍርድንና ጽድቅን ሠራሁ፤ ለሚያስጨንቁኝ አሳልፈህ አትስጠኝ።

122 ባሪያህን በመልካም ጠብቀው፤ ትዕቢተኞችም አይጋፉኝ።

123 ዓይኖቼ ለማዳንህ፥ ለጽድቅህም ቃል ፈዘዙ።

124 ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ አድርግ፥ ሥርዓትህንም አስተምረኝ።

125 እኔ ባሪያህ ነኝ፤ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ምስክርህንም አውቃለሁ።

126 ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ ነው፥ ሕግህንም ሻሩት።

127 ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቍ ይልቅ ትእዛዝህን ወደድሁ።

128 ስለዚህ ወደ ትእዛዝህ ሁሉ አቀናሁ፥ የዓመፅንም መንገድ ሁሉ ጠላሁ።

129 ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፤ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው።

130 የቃልህ ፍቺ ያበራል፥ ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል።

131 አፌን ከፈትሁ፥ አለከለክሁም፤ ወደ ትእዛዝህ ናፍቄአለሁና።

132 ስምህን ለሚወድዱ እንድምታደርገው ፍርድ፥ ወደ እኔ ተመልከተ ማረኝም።

133 አካሄድን እንደ ቃልህ አቅና፤ ኃጢአትም ሁሉ አይግዛኝ።

134 ከሰው ግፍ አድነኝ፤ ትእዛዝህንም እጠብቃለሁ።

135 በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፥ ሥርዓትህንም አሰተምረኝ።

136 ሕግህን አልጠበቅሁምና የውኃ ፈሳሽ ከዓይኖቼ ፈሰሰ።

ጻዴ

137 አቤቱ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ ፍርድህም ቅን ነው።

138 ምስክርህን በጽድቅ አዘዝህ፥ እጅግም ቅን ነው።

139 ጠላቶቼ ቃልህን ረስተዋልና የቤትህ ቅንዓት አቀለጠኝ።

140 ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፥ ባሪያህም ወደደው።

141 እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፤ ትእዛዛትህን ግን አልረሳሁም።

142 ጽድቅህ የዘላለም ጽድቅ ነው፥ ቃልህም እውነት ነው።

143 መከራና ችግር አገኙኝ፤ ትእዛዛትህ ግን ተድላዬ ናቸው።

144 ምስክርህ ለዘላለም ጽድቅ ነው፤ እንዳስተውል አድርገኝ፥ በሕይወትም አኑረኝ።

ቆፍ

145 በፍጹም ልቤ ጮኽሁ፥ አቤቱ፥ ስማኝ፤ ሥርዓትህን እፈልጋለሁ።

146 ወደ አንተ ጮኽሁ፤ አድነኝ፥ ምስክርህንም እጠብቃለሁ።

147 ማለዳ ጮኽሁ፤ ቃልህንም ተስፋ አድርጌአለሁ።

148 ቃልህን አስብ ዘንድ ዓይኖቼ ለመማለድ ቀደሙ።

149 አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ ድምፄን ስማ፤ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ።

150 በዓመፃ የሚያሳድዱኝ ቀረቡ፥ ከሕግህም ራቁ።

151 አቤቱ፥ አንተ ቅርብ ነህ፥ መንገዶችህም ሁሉ ቅኖች ናቸው።

152 ከዘላለም እንደ መሠረትኸው ከቀድሞ ጀምሮ ከምስክርህ የተነሣ አወቅሁ።

ሬስ

153 ሕግህን አልረሳሁምና ችግሬን ተመልከት አድነኝም።

154 ፍርዴን ፍረድ አድነኝም፤ ስለ ቃልህ ሕያው አድርገኝ።

155 መድኃኒት ከኅጥኣን ሩቅ ነው፥ ሥርዓትህን አልፈለጉምና።

156 አቤቱ፥ ቸርነትህ እጅግ ብዙ ነው፤ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ።

157 ያሳደዱኝና ያስጨነቁኝ ብዙዎች ናቸው፤ ከምስክር ግን ፈቀቅ አላልሁም።

158 ቃልህን አልጠበቁምና ሰነፎችን አይቼ አዘንሁ።

159 ትእዛዝህን እንደ ወደድሁ ተመልከት፤ አቤቱ፥ በምሕረትህ ሕያው አድርገኝ።

160 የቃልህ መጀመሪያ እውነት ነው፥ የጽድቅህንም ፍርድ ሁሉ ለዘላለም ነው።

ሳን

161 ገዢዎች በከንቱ አሳደዱኝ፤ ከቃልህ የተነሣ ግን ልቤ ደነገጠብኝ።

162 ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ።

163 ዓመፃን ጠላሁ ተጸየፍሁም፤ ሕግን ግን ወደድሁ።

164 ስለ ጽድቅህ ፍርድ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ።

165 ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፥ ዕንቅፋትም የለባቸውም።

166 አቤቱ፥ ማዳንህን ተስፋ አደርግሁ፥ ትእዛዛትህንም ጠበቅሁ።

167 ነፍሴ ምስክርህን ጠበቀች እጅግም ወደደችው።

168 መንገዶቼ ሁሉ በፊትህ ናቸውና ትእዛዝህንና ምስክርህን ጠበቅሁ።

ታው

169 አቤቱ፥ ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትቅረብ፤ እንደ ቃልህም አስተዋይ አድርገኝ።

170 ልመናዬ ወደ ፊትህ ትድረስ፤ እንደ ቃልህ አድነኝ።

171 ሥርዓትህን አስተምረኸኛልና ከንፈሮቼ ምስጋናን አወጡ።

172 ትእዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና አንደበቴ ቃልህን ተናገረ።

173 ትእዛዛትህን መርጫለሁና እጅህ የሚያድነኝ ይሁን።

174 አቤቱ፥ ማዳንህን ናፈቅሁ፤ ሕግህም ተድላዬ ነው።

175 ነፍሴ ትኑርልኝ ታመሰግንህማለች፥ ፍርድህም ይርዳኝ።

176 እንደ ጠፉ በግ ተቅበዘበዝሁ፤ ትእዛዛትህን አልረሳሁምና ባሪያህን ፈልገው።


መዝሙር 120

የመዓርግ መዝሙር።

1 በተጨነቅሁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ሰማኝም።

2 ከዓመፀኛ ከንፈር ከሸንጋይም አንደበት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን አድናት።

3 ስለ ሽንገላ አንደበት ምንም ይሰጡሃል? ምንስ ይጨምሩልሃል?

4 እንደ በረሃ እንጨት ፍም የኃያላን ፍላጾች የተሳሉ ናቸው።

5 መኖሪያዬ የራቀ እኔ ወዮልኝ፤ በቄዳር ድንኳኖች አደርሁ።

6 ሰላምን ከሚጠሉ ጋር ነፍሴ ብዙ ጊዜ ኖረች።

7 እኔ ሰላማዊ ነኝ፤ በተናገኋቸው ጊዜ ግን በከንቱ ተሰለፉብኝ።


መዝሙር 121

የመዓርግ መዝሙር።

1 ዓይኖቼ ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ?

2 ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

3 እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም።

4 እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም።

5 እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል።

6 ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት።

7 እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል።

8 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል።


መዝሙር 122

የዳዊት የመዓርግ መዝሙር።

1 ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሄድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ።

2 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ እግሮቻችን በአደባባይሽ ቆሙ።

3 ኢየሩሳሌምስ እርስ በርስዋ እንደ ተገጠገጠች ከተማ ተሠርታለች።

4 የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ ዘንድ፥ ለእስራኤል ምስክር ሊሆኑ የእግዚአብሔር ነገዶች ወደዚያ ይወጣሉ።

5 ዙፋኖች በዚያ ለፍርድ ተቀምጠዋልና፥ የዳዊት ቤት ዙፋኖች።

6 ለኢየሩሳሌም ሰላምን ለምኑ፤ አንተንም ለሚወድዱ ልማት ይሁን።

7 በኃይልህ ሰላም፥ በጌጠኛ ቤትህም ልማት ይሁን።

8 ስለ ወንድሞቼ ስለ ባልንጀሮቼም፥ በውስጥሽ ሰላም ይሁን አልሁ።

9 ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት ላንቺ መልካምነትሽን ፈለግሁ።


መዝሙር 123

የመዓርግ መዝሙር።

1 በሰማይ የምትኖር ሆይ፥ ዓይኖቼን ወደ አንተ አነሣሁ።

2 እነሆ፥ የባሪያዎች ዓይኖች ወደ ጌታቸው እጅ እንደ ሆኑ፥ የባሪያይቱም ዓይን ወደ እመቤትዋ እጅ እንደ ሆነ፥ እንዲሁ እስኪምረን ድረስ ዓይናችን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ነው።

3 ማረን፥ አቤቱ፥ ማረን፤ ንቀትን እጅግ ጠግበናልና፤

4 የባለጠጎች ስድብና የትዕቢተኞችን ንቀት ነፍሳችን እጅግ ጠገበች።


መዝሙር 124

የዳዊት የመዓርግ መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን እስራኤል እንዲህ ይበል።

2 እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ፥

3 ቍጣቸውን በላያችን በነደደ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር፤

4 በዚያን ጊዜ ውኃ ባሰጠመን ነበር፥ በነፍሳችንም ላይ ፈሳሽ ባለፈ ነበር፤

5 በዚያን ጊዜ የጐርፍ ውኃ በነፍሳችን ላይ ባለፈ ነበር።

6 ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን እግዚአብሔር ይባረክ።

7 ነፍሳችን እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች። ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን።

8 ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በእግዚአብሔር ስም ነው።


መዝሙር 125

የመዓርግ መዝሙር።

1 በእግዚአብሔር የታመኑ እንደማይታወክ ለዘላለም እንደሚኖር እንደ ጽዮን ተራራ ናቸው።

2 ተራሮች በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ሆኑ፥ ከዛሬ ጀምሮ ለዘላለም፤ እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው።

3 ጻድቃን እጃቸውን ወደ ክፋት እንዳይዘረጉ የኃጥኣን በትር በጻድቃን ዕጣ ላይ አይኖርም።

4 አቤቱ፥ ለቸሮች ልባቸውም ለቀና መልካምን አድርግ።

5 ወደ ጠማማነት የሚመለሱትን ግን ዓመፃን ከሚሠሩት ጋር እግዚአብሔር ይወስዳቸዋል። ሰላም በእስራኤል ላይ ይሁን።


መዝሙር 126

የመዓርግ መዝሙር።

1 እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ እጅግ ደስተኞች ሆንን።

2 በዚያን ጊዜ አፋችን ደስታን፥ አንደበታችንም ሐሴትን ሞላ፤ በዚያን ጊዜ በአሕዛብ ዘንድ። እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገላቸው ተባለ።

3 እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገልን፥ ደስም አለን።

4 አቤቱ፥ በደቡብ እንዳሉ ፈሳሾች ምርኮአችንን መልስ።

5 በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ።

6 በሄዱ ጊዜ፥ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ።


መዝሙር 127

የመዓርግ መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል።

2 በማለዳ መገሥገሣችሁም ከንቱ ነው። ለወዳጆቹ እንቅልፍን በሰጠ ጊዜ፥ እናንተ የመከራን እንጀራ የምትበሉ፥ ከተቀመጣችሁበት ተነሡ።

3 እነሆ፥ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፥ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው።

4 በኃያል እጅ እንዳሉ ፍላጾች፥ የጐልማስነት ልጆች እንዲሁ ናቸው።

5 ከእነርሱ ዘንድ ምኞቱን የሚፈጽም ብፁዕ ሰው ነው፤ ጠላቶቻቸውን በአደባባይ በተናገሩ ጊዜ እርሱ አያፍርም።


መዝሙር 128

የመዓርግ መዝሙር።

1 እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሁሉ፥ በመንገዶቹም የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው።

2 የድካምህንም ፍሬ ትመገባለህ፤ ምስጉን ነህ መልካምም ይሆንልሃል።

3 ሚስትህ በቤትህ እልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት፤ ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው።

4 እነሆ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንዲህ ይባረካል።

5 እግዚአብሔር ከጽዮን ይባርክህ፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ የኢየሩሳሌምን መልካምነትዋን ታያለህ።

6 የልጆችህንም ልጆች ታያለህ። በእስራኤል ላይ ሰላም ይሁን።


መዝሙር 129

የመዓርግ መዝሙር።

1 እስራኤል። ከትንሽነቴ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ተሰለፉብኝ ይበል፤

2 ከትንሽነቴ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ተሰለፉብኝ፤ ነገር ግን አላሸነፉኝም።

3 ኃጢአተኞች በጀርባዬ ላይ መቱኝ፥ ኃጢአታቸውንም አስረዘሙአት።

4 እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤ የኃጢአተኞችን አንገታቸውን ቈረጠ።

5 ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ፥ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ።

6 በሰገነት ላይ እንደ በቀለ ሣር፥ ሳይነቀል እንደሚደርቅ፥

7 ለሚያጭደው እጁን፥ ነዶዎቹን ለሚሰበስብ እቅፉን እንደማይሞላ ይሁኑ።

8 በመንገዱም የሚያልፉ። የእግዚአብሔር በረከት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በእግዚአብሔር ስም እንመርቃችኋለን አይሉም።


መዝሙር 130

የመዓርግ መዝሙር።

1 አቤቱ፥ አንተን ከጥልቅ ጠራሁህ።

2 አቤቱ፥ ድምፄን ስማ፤ ጆሮህ የልመናዬን ቃል የሚያደምጥ ይሁን።

3 አቤቱ፥ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፥ አቤቱ፥ ማን ይቆማል?

4 ይቅርታ ከአንተ ዘንድ ነውና።

5 አቤቱ፥ ስለ ስምህ ተስፋ አደረግሁህ፤ ነፍሴ በሕግህ ታገሠች።

6 ከማለዳው ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ነፍሴ በእግዚአብሔር ታመነች።

7 ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን ነውና እስራኤል በእግዚአብሔር ይታመን።

8 እርሱም እስራኤልን ከኃጢአቱ ሁሉ ያድነዋል።


መዝሙር 131

የዳዊት መዓርግ መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ልቤ አይታበይብኝ፥ ዓይኖቼም ከፍ ከፍ አይበሉብኝ፤ ከትልልቆች ጋር፥ ከእኔም ይበልጥ ከሚከበሩ ጋር አልሄድሁም።

2 ነፍሴን አሳረፍኋት፥ የእናቱንም ጡት እንዳስተውት ዝም አሰኘኋት፤ ነፍሴ የእናቱን ጡት እንዳስተውት በእኔ ውስጥ ናት።

3 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እስራኤል በእግዚአብሔር ይታመን።


መዝሙር 132

የመዓርግ መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ዳዊትን ገርነቱንም ሁሉ አስብ፤

2 ለእግዚአብሔር እንደ ማለ፥ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ።

3 በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ ምንጣፌም አልጋ አልወጣም፥

4 ለዓይኖቼም መኝታ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ፥ ለጕንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፥

5 ለእግዚአብሔር ስፍራ፥ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ።

6 እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው።

7 ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን።

8 አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።

9 ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ፥ ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው።

10 ስለ ዳዊት ስለ ባሪያህ የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ።

11 እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ አይጸጸትምም፥ እንዲህ ብሎ። ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ።

12 ልጆችህ ኪዳኔን፥ ይህንም የማስተምራቸውን ምስክሬን ቢጠብቁ፥ ልጆቻቸው ደግሞ በዙፋንህ ላይ ለዘላለም ይቀመጣሉ።

13 እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ።

14 ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ።

15 አሮጊቶችዋን እጅግ እባርካለሁ፥ ድሆችዋንም እንጀራ አጠግባለሁ።

16 ካህናቶችዋንም ደኅንነትን አለብሳቸዋለሁ፥ ቅዱሳኖችዋም እጅግ ደስ ይላቸዋል።

17 በዚያ ለዳዊት ቀንድን አበቅላለሁ፥ ለቀባሁትም ሰው መብራትን አዘጋጃለሁ።

18 ጠላቶችንም እፍረትን አለብሳቸዋለሁ፤ በእርሱ ግን ቅድስናዬ ያብባል።


መዝሙር 133

የዳዊት የመዓርግ መዝሙር።

1 ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው።

2 ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው።

3 በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና።


መዝሙር 134

የመዓረግ መዝሙር።

1 እነሆ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ፥ በአምላካችን ቤት አደባባዬች የምትቆሙ እናንተ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሁላችሁ።

2 በሌሊት በቤተ መቅደስ ውስጥ እጆቻችሁን አንሡ፥ እግዚአብሔርንም ባርኩ።

3 ሰማይንና ምድርን የሠራ እግዚአብሔር ከጽዮን ይባርክህ።


መዝሙር 135

1 ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔርን ስም አመስግኑ፤ እናንተ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥

2 በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ፥ በአምላካችን ቤት አደባባይ የምትቆሙ።

3 እግዚአብሔር ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ለስሙ ዘምሩ፥ መልካም ነውና፤

4 እግዚአብሔር ያዕቆብን ለራሱ፥ እስራኤልንም ለመዝገቡ መርጦታልና፤

5 እግዚአብሔር ታላቅ እንደ ሆነ፥ ጌታችንም ከአማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አውቄአለሁና።

6 በሰማይና በምድር በባሕርና በጥልቆች ሁሉ፥ እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ።

7 ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል፤ በዝናብ ጊዜ መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳትንም ከመዛግብቱ ያወጣል።

8 የግብጽን በኵር ልጆች ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ መታ።

9 ግብጽ ሆይ፥ በመካከልሽ በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ ላይ ተኣምራትንና ድንቅን ሰደደ።

10 ብዙ አሕዛብን መታ፥ ብርቱዎችንም ነገሥታት ገደለ።

11 የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ የባሳንንም ንጉሥ ዐግን፥ የከነዓንን መንግሥታት ሁሉ ገደለ፤

12 ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ለእስራኤል ለሕዝቡ ርስት ሰጠ።

13 አቤቱ፥ ስምህ ለዘላለም ነው፥ ዝክርህም ለልጅ ልጅ ነው፤

14 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳልና፥ ባሪያዎቹንም ይረዳልና።

15 የአሕዛብ ጣዖታት የብርና የወርቅ፥ የሰው እጅ ሥራ ናቸው።

16 አፍ አላቸው፥ አይናገሩምም፤ ዓይን አላቸው፥ አያዩምም፤

17 ጆሮ አላቸው፥ አይሰሙምም፤ እስትንፋስም በአፋቸው የለም።

18 የሚሠሩአቸው ሁሉ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁን።

19 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት። የአሮን ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት፤

20 የሌዊ ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት።

21 በኢየሩሳሌም የሚያድር እግዚአብሔር ከጽዮን የተባረከ ነው። ሃሌ ሉያ።


መዝሙር 136

1 እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።

2 የአማልክትን አምላክ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።

3 የጌቶችን ጌታ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

4 እርሱ ብቻውን ታላቅ ተኣምራትን ያደረገ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

5 ሰማያትን በብልሃት የሠራ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

6 ምድርን በውኃ ላይ ያጸና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

7 ብቻውን ታላላቅ ብርሃናትን የሠራ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

8 ለፀሐይ ቀንን ያስገዛው፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

9 ለጨረቃና ለከዋክብትም ሌሊትን ያስገዛቸው፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

10 ከበኵራቸው ጋር ግብጽን የመታ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

11 እስራኤልንም ከመካከላቸው ያወጣ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

12 በጸናች እጅ በተዘረጋችም ክንድ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

13 የኤርትራን ባሕር በየክፍሉ የከፈለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

14 እስራኤልን በመካከሉ ያሳለፈ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

15 ፈርዖንንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር የጣለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

16 ሕዝቡን በምድረ በዳ የመራ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

17 ታላላቅ ነገሥታትን የመታ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

18 ብርቱዎችንም ነገሥታት የገደለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

19 የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

20 የባሳንን ንጉሥ ዐግን፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

21 ምድራቸውን ርስት አድርጎ የሰጠ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

22 ለባሪያው ለእስራኤል ርስት፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።

23 እኛን በመዋረዳችን አስቦናልና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

24 ከጠላቶቻችንም እጅ አድኖናልና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

25 ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።

26 የሰማይን አምላክ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።


መዝሙር 137

1 በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን።

2 በአኻያ ዛፎችዋ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን።

3 የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፥ የወሰዱንም። የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን።

4 የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?

5 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥ ቀኜ ትርሳኝ።

6 ባላስብሽ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ።

7 አቤቱ፥ በኢየሩሳሌም ቀን የኤዶምን ልጆች አስብ። እስከ መሠረትዋ ድረስ አፍርሱ አፍርሱ ያሉአትን።

8 አንቺ ወራዳ የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ስለ ተበቀልሽን የሚበቀልሽ የተመሰገነ ነው።

9 ሕፃናቶችሽን ይዞ በዓለት ላይ የሚፈጠፍጣቸው የተመሰገነ ነው።


መዝሙር 138

የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ የአፌን ነገር ሰምተኸኛልና፤ በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ።

2 ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ምሕረትህና ስለ እውነትህ ስምህንም አመሰግናለሁ፥ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሃልና።

3 በጠራሁህ ቀን በፍጥነት አድምጠኝ፤ ነፍሴን በኃይልህ በብዙ አጸናሃት።

4 አቤቱ፥ የምድር ነገሥታት ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ የአፍህን ቃል ሁሉ ሰምተዋልና።

5 በእግዚአብሔርም መንገድ ይዘምራሉ፤ የእግዚአብሔር ክብር ታላቅ ነውና።

6 እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና፥ ወደ ችግረኞችም ይመለከታልና፤ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል።

7 በመከራ መካከል እንኳ ብሄድ፥ አንተ ሕያው ታደርገኛለህ፤ በጠላቶቼ ቍጣ ላይ እጆቼን ትዘረጋለህ፥ ቀኝህም ታድነኛለች።

8 እግዚአብሔር ብድራትን ይመልስልኛል፤ አቤቱ፥ ምሕረትህ ለዘላለም ነው፤ አቤቱ፥ የእጅህን ሥራ ቸል አትበል።


መዝሙር 139

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም።

2 አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፤ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ።

3 ፍለጋዬንና ዕረፍቴን አንተ መረመርህ፤ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ፥

4 የዓመፃ ቃል በአንደበቴ እንደሌለ።

5 አቤቱ፥ አንተ እነሆ የቀድሞውንና የኋላውን አወቅህ፤ አንተ ፈጠርኸኝ፥ እጅህንም በላዬ አደረግህ።

6 እውቀትህ ከእኔ ይልቅ ተደነቀች፤ በረታች፥ ወደ እርስዋም ለመድረስ አልችልም።

7 ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?

8 ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ።

9 እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥

10 በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች።

11 በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትሆናለች፤

12 ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው።

13 አቤቱ፥ አንተ ኵላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል።

14 ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።

15 እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም።

16 ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።

17 አቤቱ፥ አሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደ ምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቍጥራቸውም እንደ ምን በዛ!

18 ብቈጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ፤ ተነሣሁም፥ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ።

19 አቤቱ፥ አንተ ኃጢአተኞችን የምትገድል ከሆንህስ፥ የደም ሰዎች ሆይ፥ ከእኔ ፈቀቅ በሉ።

20 በክፋት ይናገሩብሃልና፤ ጠላቶችህም በከንቱ ያምፁብሃል።

21 አቤቱ፥ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? ስለ ጠላቶችህም አልተሰቀቅሁምን?

22 ፍጹም ጥል ጠላኋቸው፥ ጠላቶችም ሆኑኝ።

23 አቤቱ፥ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ ፍተነኝ መንገዴንም እወቅ፤

24 በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፤ የዘላለምንም መንገድ ምራኝ።


መዝሙር 140

ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር።

1-2 አቤቱ፥ ከክፉ ሰው አድነኝ፥ በልባቸውም ክፉ ካሰቡ ከዓመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ፤ ቀኑን ሁሉ ለሰልፍ ይከማቻሉ።

3 ምላሳቸውን እንደ እባብ ሳሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእፉኝት መርዝ ነው።

4 አቤቱ፥ ከኃጢአተኞች እጅ ጠብቀኝ፥ እርምጃዬንም ሊያሰናክሉ ከመከሩ ከዓመፀኞች አድነኝ።

5 ትዕቢተኞች ወጥመድን ሰወሩብኝ፥ ለእግሮቼም የወጥመድ ገመድን ዘረጉ፤ በመንገድ ዕንቅፋትን አኖሩ።

6 እግዚአብሔርንም። አንተ አምላኬ ነህ፤ የልመናዬን ቃል፥ አቤቱ፥ አድምጥ አልሁት።

7 አቤቱ፥ ጌታዬ፥ የመድኃኒቴ ጕልበት፥ በሰልፍ ቀን ራሴን ሸፈንህ።

8 አቤቱ፥ ከምኞቴ የተነሣ ለኃጢአተኞች አትስጠኝ፤ በላዬ ተማከሩ፤ እንዳይጓደዱ አትተወኝ።

9 የሚከብቡኝን ራስ የከንፈራቸው ክፋት ይክደናቸው።

10 የእሳት ፍም በላያቸው ይውደቅ፤ እንዳይነሡም ወደ እሳትና ወደ ማዕበል ይጣሉ።

11 ተናጋሪ ሰው በምድር ውስጥ አይጸናም፤ ዓመፀኛን ሰው ክፋት ለጥፋት ይፈልገዋል።

12 እግዚአብሔር ለድሀ ዳኝነትን ለችግረኛም ፍርድን እንዲያደርግ አወቅሁ።

13 ጻድቃንም በእውነት ስምህን ያመሰግናሉ፤ ቀኖችም በፊትህ ይኖራሉ።


መዝሙር 141

የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ ስማኝ፤ ወደ አንተ ስጮኽም የልመናዬን ቃል አድምጥ።

2 ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጅ መንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን።

3 አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ።

4 ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው፥ ዓመፃን ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ለኃጢአት ምክንያት እንዳልሰጥ፤ ከምርጦቻቸውም ጋር አልተባበር።

5 ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ፥ ይዝለፈኝም፥ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ፤ ጸሎቴ ገና በክፋታቸው ላይ ነውና።

6 ኃያላኖቻቸው በዓለት አጠገብ ተጣሉ፤ ጣፋጭ ናትና ቃሌን ይሰማሉ።

7 በምድር ላይ እንደ ተሰነጠቀ እንደ መሬት ጓል፥ እንዲሁ አጥንቶቻችን በሲኦል ተበተኑ።

8 አቤቱ ጌታ፥ ዓይኖቼ ወደ አንተ ናቸውና፤ በአንተ ታመንሁ፥ ነፍሴን አታውጣት።

9 ከሰወሩብኝ ወጥመድ፥ ዓመፅንም ከሚያደርጉ ሰዎች ዕንቅፋት ጠብቀኝ።

10 እኔ ብቻዬን እስካልፍ ድረስ ኃጢአተኞች በወጥመዳቸው ይውደቁ።


መዝሙር 142

ጸሎት፤ በዋሻ በነበረ ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት።

1 በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፤ በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ለመንሁ።

2 ልመናዬን በፊቱ አፈስሳለሁ፤ መከራዬንም በፊቴ እናገራለሁ።

3 ነፍሴ በውስጤ ባለቀች ጊዜ መንገዴን አወቅሁ፤ በምሄድባት በዚያች መንገድ ወጥመድን ሰወሩብኝ።

4 ወደ ቀኝ ተመለከትሁ አየሁም፥ የሚያውቀኝም አጣሁ፤ መሸሸጊያም የለኝም፥ ስለ ነፍሴም የሚመራመር የለም።

5 አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ። አንተ ተስፋዬ ነህ፥ በሕያዋንም ምድር አንተ እድል ፈንታዬ ነህ አልሁ።

6 እጅግ ተቸግሬአለሁና ወደ ልመናዬ አድምጥ፤ በርትተውብኛልና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ።

7 አቤቱ፥ ስምህን አመሰግን ዘንድ፤ ነፍሴን ከወህኒ አውጣት፤ ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ።


መዝሙር 143

ልጁ ባሳደደው ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፤ በእውነትህ ልመናዬን አድምጥ፥ በጽድቅህም መልስልኝ።

2 ሕያው ሁሉ በፊትህ ጻድቅ አይደለምና ከባሪያህ ጋር ወደ ፍርድ አትግባ።

3 ጠላትህ ነፍሴን አሳድዶአታል፥ ሕይወቴንም በምድር ውስጥ አጐስቍሎአታል፤ ቀድሞ እንደ ሞተ ሰው በጨለማ አኑሮኛል።

4 ነፍሴ በውስጤ አለቀችብኝ፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ።

5 የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፥ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ ተመለከትሁ።

6 እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፤ ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች።

7 አቤቱ፥ ፈጥነህ ስማኝ፤ ነፍሴ አልቃለች፤ ፊትህን ከኔ አትመልስ፥ ወደ ጕድጓድም እንደሚወርዱ አልሁን።

8 አንተን ታምኛለሁና በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አስታውቀኝ።

9 አቤቱ፥ ወደ አንተ ተማፅኛለሁና ከጠላቶቼ አድነኝ።

10 አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፤ ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ።

11 አቤቱ፥ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፤ በጽድቅህም ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት።

12 በምሕረትህ ጠላቶቼን ደምስሳቸው፥ እኔ ባሪያህ ነኝና ነፍሴን የሚያስጨንቁአትን ሁሉ አጥፋቸው።


መዝሙር 144

ስለ ጎልያድ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር አምላኬ ይባረክ፥ ለእጆቼ ሰልፍን፥ ለጣቶቼም ዘመቻን የሚያስተምር፤

2 መሓሪዬና መሸሸጊያዬ፥ መጠጊያዬና መድኃኒቴ፤ ረዳቴና መታመኛዬም፤ ሕዝቤንም ከእኔ በታች የሚያስገዛልኝ።

3 አቤቱ፥ እርሱን ታውቀው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ታስብለት ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?

4 ሰው ከንቱን ነገር ይመስላል፤ ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል።

5 አቤቱ፥ ሰማዮችህን ዝቅ ዝቅ አድርጋቸው ውረድም፤ ተራሮችን ዳስሳቸው ይጢሱም።

6 መብረቆችህን ብልጭ አድርጋቸው በትናቸውም፤ ፍላጾችህን ላካቸው አስደንግጣቸውም።

7-8 እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም ከብዙ ውኆች፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ።

9 አቤቱ፥ አዲስ ቅኔ እቀኛልሃለሁ፤ አሥር አውታር ባለው በገና እዘምርልሃለሁ።

10 ለነገሥታት መድኃኒትን የሚሰጥ፥ ባሪያውን ዳዊትን ከክፉ ሰይፍ የሚያድነው እርሱ ነው።

11 አድነኝ፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸውም የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ።

12 ልጆቻቸው በጕልማስነታቸው እንደ አዲስ አትክልት የሆኑ፥ ሴቶች ልጆቻቸውም እንደ እልፍኝ ያማሩና ያጌጡ፤

13 ዕቃ ቤቶቻቸውም የተሞሉ በየዓይነቱ ዕቃ የሚሰጡ፥ በጎቻቸውም ብዙ የሚወልዱ፥ በማሰማርያቸውም የሚበዙ፥

14 ላሞቻቸውም የሚሰቡ፤ ቅጥራቸውም መፍረሻና መውጫ የሌለው፥ በአደባባዮቻቸውም ዋይታ የሌለ፤

15 እንደዚህ የሚሆን ሕዝብ የተመሰገነ ነው፤ እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው።


መዝሙር 145

የዳዊት የምስጋና መዝሙር።

1 አምላኬ ንጉሤ ሆይ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፥ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም እባርካለሁ።

2 በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ።

3 እግዚአብሔር ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም።

4 ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፥ ኃይልህንም ያወራሉ።

5 የቅድስናህን ግርማ ክብር ይናገራሉ፥ ተኣምራትህንም ይነጋገራሉ።

6 የግርማህንም ኃይል ይናገራሉ፥ ታላቅነትህንም ይነጋገራሉ፥ ብርታትህንም ይነጋገራሉ።

7 የቸርነትህን ብዛት መታሰብ ያወጣሉ፥ በጽድቅህም ሐሤትን ያደርጋሉ።

8 እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ ነው፥ ከቍጣ የራቀ፥ ምሕረቱም ብዙ ነው፤

9 እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር ነው። ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ነው።

10 አቤቱ፥ ሥራህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፥ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል።

11 የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ፥ ኃይልህንም ይነጋገራሉ፥

12 ለሰው ልጆች ኃይልህን የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ

13 መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው።

14 እግዚአብሔር በቃሎቹ የታመነ ነው፥ በሥራውም ሁሉ ጻድቅ ነው፤ እግዚአብሔር የተፍገመገሙትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፥ የወደቁትንም ያነሣቸዋል።

15 የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ።

16 አንተ እጅህን ትከፍታለህ፥ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ።

17 እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።

18 እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፥ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።

19 ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፥ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም።

20 እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል።

21 አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤ ሥጋም ሁሉ ለዘላለም ዓለም የተቀደሰውን ስሙን ይባርክ።


መዝሙር 146

የሐጌና የዘካርያስ መዝሙር።

1 ሃሌ ሉያ። ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን አመስግኚ።

2 በሕይወቴ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በምኖርበት ዘመን ሁሉ ለአምላኬ እዘምራለሁ።

3 ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ።

4 ነፍሱ ትወጣለች ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል።

5 የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውም በአምላኩ በእግዚአብሔር የሆነ ሰው ምስጉን ነው፤

6 እርሱም ሰማይንና ምድርን ባሕርንም፥ በእነርሱ ያለውንም ሁሉ የፈጠረ፤ እውነትን ለዘላለም የሚጠብቅ፤

7 ለተበደሉት የሚፈርድ፥ ለተራቡ ምግብን የሚሰጥ ነው። እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል፤

8 እግዚአብሔር የወደቁትን ያነሣል፤ እግዚአብሔር ዕውሮችን ጥበበኞች ያደርጋቸዋል፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤

9 እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድሀ አደጎችንና ባልቴቶችን ይቀበላል፤ የኃጢአተኞችንም መንገድ ያጠፋል።

10 እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ ጽዮን ሆይ፥ አምላክሽ ለልጅ ልጅ ነው። ሃሌ ሉያ።


መዝሙር 147

የሐጌና የዘካርያስ መዝሙር።

1 እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ መዝሙር መልካም ነውና። ለአምላካችን ምስጋና ያማረ ነው።

2 እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይሠራል፥ ከእስራኤልም የተበተኑትን ይሰበስባል።

3 ልባቸውን የቈሰሉትን ይፈውሳል፥ ሕማማቸውንም ይጠግናል።

4 የከዋክብትንም ብዛት ይቈጥራል፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።

5 ጌታችን ታላቅ ነው፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ ለጥበቡም ቍጥር የለውም።

6 እግዚአብሔር የዋሃንን ያነሣል፥ ኃጢአተኞችን ግን እስከ ምድር ድረስ ያዋርዳል።

7 ለእግዚአብሔር በምስጋና ዘምሩ፥ ለአምላካችንም በመሰንቆ ዘምሩ፤

8 ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል ለምድርም ዝናብን ያዘጋጃል፤ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም።

9 ለሚጠሩት ለቍራዎች ጫጩቶች ለእንስሶችም ምግባቸውን ይሰጣል።

10 የፈረስን ኃይል አይወድድም፥ በሰውም ጭን አይደሰትም።

11 እግዚአብሔር በሚፈሩት፥ በምሕረቱም በሚታመኑት ይደሰታል።

12 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ እግዚአብሔርን አመስግኚ፥

13 ጽዮንም ሆይ፥ ለአምላክሽ እልል በዪ፤ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቶአልና፥ ልጆችንም በውስጥሽ ባርኮአልና።

14 በወሰንሽም ሰላምን አደረገ፥ የስንዴንም ስብ አጠገበሽ።

15 ነገሩን ወደ ምድር ይሰድዳል፥ ቃሉም እጅግ ፈጥኖ ይሮጣል።

16 አመዳዩን እንደ ባዘቶ ይሰጣል፤ ጉሙን እንደ አመድ ይበትነዋል፤

17 በረዶውን እንደ ፍርፋሪ ያወርዳል፤ በበረዶውስ ፊት ማን ይቆማል?

18 ቃሉን ልኮ ያቀልጠዋል፤ ነፋሱን ያነፍሳል፥ ውኆችንም ያፈስሳል።

19 ቃሉን ለያዕቆብ፥ ሥርዓቱንና ፍርዱን ለእስራኤል ይናገራል።

20 ለሌሎች አሕዛብ ሁሉ እንዲህ አላደረገም፥ ፍርዱንም አልገለጠላቸውም። ሃሌ ሉያ።


መዝሙር 148

የሐጌና የዘካርያስ መዝሙር።

1 ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን ከሰማያት አመስግኑት፤ በአርያም አመስግኑት።

2 መላእክቱ ሁሉ፥ አመስግኑት፤ ሠራዊቱ ሁሉ፥ አመስግኑት።

3 ፀሐይና ጨረቃ፥ አመስግኑት፤ ከዋክብትና ብርሃን ሁሉ፥ አመስግኑት።

4 ሰማየ ሰማያት፥ አመስግኑት የሰማያት በላይም ውኃ።

5 እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት።

6 ለዘላለም ዓለም አቆማቸው፤ ትእዛዝን ሰጠ፥ አያልፉምም።

7 እባቦች ጥልቆችም ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት፤

8 እሳትና በረዶ አመዳይና ውርጭ፥ ቃሉን የሚያደርግ ዐውሎ ነፋስም፤

9 ተራሮች ኰረብቶችም ሁሉ፥ የሚያፈራም ዛፍ ዝግባም ሁሉ፤

10 አራዊትም እንስሳትም ሁሉ፥ ተንቀሳቃሾችም የሚበርሩ ወፎችም፤

11 የምድር ነገሥታት አሕዛብም ሁሉ፥ አለቆች የምድርም ፈራጆች ሁሉ፥

12 ጕልማሶችና ቈነጃጅቶች፥ ሽማግሌዎችና ልጆች፤

13 የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ፤ ስሙ ብቻውን ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ ምስጋናውም በሰማይና በምድር ላይ ነው።

14 የሕዝቡንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ የቅዱሳኑንም ሁሉ ምስጋና ወደ እርሱ ለቀረበ ለእስራኤል ልጆች ሕዝብ ከፍ ከፍ ያደርጋል። ሃሌ ሉያ።


መዝሙር 149

1 ሃሌ ሉያ። ለእግዚአብሔር አዲሱን ቅኔ ተቀኙለት፤ ምስጋናው በቅዱሳኑ ጉባኤ ነው።

2 እስራኤል በፈጣሪው ደስ ይበለው፥ የጽዮንም ልጆች በንጉሣቸው ሐሤትን ያድርጉ።

3 ስሙን በዘፈን ያመስግኑ፥ በከበሮና በመሰንቆም ይዘምሩለት።

4 እግዚአብሔር በሕዝቡ ተደስቶአልና፥ የዋሃንንም በማዳኑ ከፍ ከፍ ያደርጋልና።

5 ቅዱሳን በክብር ይመካሉ፤ በምንጣፋቸውም ላይ ሐሤትን ያደርጋሉ።

6 የእግዚአብሔር ምስጋና በጕሮሮአቸው ነው፤ ሁለት አፍ ያለውም ሰይፍ በእጃቸው ነው፥

7 በአሕዛብ ላይ በቀልን በሰዎችም መካከል ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ፤

8 ንጉሦቻቸውን በሰንሰለት፥ አለቆቻቸውንም በእግር ብረት ያስሩ ዘንድ፤

9 የተጻፈውን ፍርድ ያደርጉባቸው ዘንድ። ለቅዱሳን ሁሉ ይህች ክብር ናት። ሃሌ ሉያ።


መዝሙር 150

1 ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን በመቅደሱ አመስግኑት፤ በኃይሉ ጠፈር አመስግኑት።

2 በችሎቱ አመስግኑት፤ በታላቅነቱ ብዛት አመስግኑት።

3 በመለከት ድምፅ አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት።

4 በከበሮና በዘፈን አመስግኑት፤ በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት።

5 ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት፤ እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት።

6 እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን። ሃሌ ሉያ።