መዝሙር 1

1 ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ።

2 ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።

3 እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።

4 ክፉዎች እንዲህ አይደሉም፥ ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው።

5 ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ፥ ኃጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር አይቆሙም።

6 እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፥ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች።


መዝሙር 2

1 አሕዛብ ለምን ያጕረመርማሉ? ወገኖችስ ለምን ከንቱን ይናገራሉ?

2 የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ።

3 ማሰርያቸውን እንበጥስ፥ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል።

4 በሰማይ የሚኖር እርሱ ይሥቃል፥ ጌታም ይሣለቅባቸዋል።

5 በዚያን ጊዜ በቍጣው ይናገራቸዋል፥ በመዓቱም ያውካቸዋል።

6 እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ።

7 ትእዛዙን እናገራለሁ፤ እግዚአብሔር አለኝ። አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።

8 ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ።

9 በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃዎች ትቀጠቅጣቸዋለህ።

10 አሁንም እናንት ነገሥታት፥ ልብ አድርጉ፤ እናንት የምድር ፈራጆችም፥ ተገሠጹ።

11 ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ።

12 ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቈጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፥ ቍጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው።


መዝሙር 3

ከልጁ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸ ጊዜ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ የሚያስጨንቁኝ ምንኛ በዙ! በኔ ላይ የሚቆሙት ብዙ ናቸው።

2 ብዙ ሰዎች ነፍሴን። አምላክሽ አያድንሽም አልዋት።

3 አንተ ግን አቤቱ፥ መጠጊያዬ ነህ፥ ክብሬንና ራሴንም ከፍ ከፍ የምታደርገው አንተ ነህ።

4 በቃሌ ወደ እግዚአብሔር እጮሃለሁ ከተቀደሰ ተራራውም ይሰማኛል።

5 እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም፤ እግዚአብሔርም ደግፎኛልና ነቃሁ።

6 ከሚከብቡኝ ከአእላፍ ሕዝብ አልፈራም።

7 ተነሥ፥ አቤቱ፤ አምላኬ ሆይ፥ አድነኝ፤ አንተ የጠላቶቼን መንጋጋ መትተሃልና፥ የክፉዎችንም ጥርስ ሰብረሃልና።

8 ማዳን የእግዚአብሔር ነው፥ በረከትህም በሕዝብህ ላይ ነው።


መዝሙር 4

ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች፤ የዳዊት መዝሙር።

1 የጽድቄ አምላክ በጠራሁት ጊዜ መለሰልኝ፥ በጭንቀቴም አሰፋህልኝ፤ ማረኝ፥ ጸሎቴንም ስማ።

2 እናንት የሰው ልጆች፥ እስከ መቼ ድረስ ልባችሁን ታከብዳላችሁ?

3 እግዚአብሔር በጻድቁ እንደ ተገለጠ እወቁ፤ እግዚአብሔር ወደ እርሱ በተጣራሁ ጊዜ ይሰማኛል።

4 ተቈጡ፥ ነገር ግን ኃጢአትን አታድርጉ፤ በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ አስቡ፤ ዝም በሉ።

5 የጽድቅን መሥዋዕት ሠዉ፥ በእግዚአብሔርም ታመኑ።

6 በጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙ ናቸው። አቤቱ፥ የፊትህ ብርሃን በላያችን ታወቀ።

7 በልቤ ደስታን ጨመርህ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ከዘይትም ይልቅ በዛ።

8 በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ፥ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና።


መዝሙር 5

ለመዘምራን አለቃ በዋሽንት፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ቃሌን አድምጥ፥ ጩኸቴንም አስተውል፤

2 የልመናዬን ቃል አድምጥ፥ ንጉሤና አምላኬ ሆይ፥ አቤቱ፥ ወደ አንተ እጸልያለሁና።

3 በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ፥ በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ፥ እጠብቃለሁም።

4 አንተ በደልን የማትወድድ አምላክ ነህና፤ ክፉ ከአንተ ጋር አያድርም።

5 በከንቱ የሚመኩ በዓይኖችህ ፊት አይኖሩም፤ ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ።

6 ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ፤ ደም አፍሳሹንና ሸንጋዩን ሰው እግዚአብሔር ይጸየፋል።

7 እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ።

8 አቤቱ፥ ስለ ጠላቶቼ በጽድቅህ ምራኝ፤ መንገዴን በፊትህ አቅና።

9 በአፋቸው እውነት የለምና፥ ልባቸውም ከንቱ ነው፤ ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ይሸነግላሉ።

10 አቤቱ፥ ፍረድባቸው፥ በምክራቸውም ይውደቁ፤ ስለ ክፋታቸውም ብዛት አሳድዳቸው፥ እነርሱ ዐምፀውብሃልና።

11 በአንተ የሚታመኑት ሁሉ ግን ደስ ይላቸዋል፤ ለዘላለሙ ደስ ይላቸዋል፥ እነርሱንም ትጠብቃለህ፤ ስምህንም የሚወድዱ ሁሉ በአንተ ይመካሉ።

12 አንተ ጻድቁን ትባርከዋለህና፤ አቤቱ፥ እንደ ጋሻ በሞገስ ከለልኸን።


መዝሙር 6

ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች ስለ ስምንተኛ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ።

2 ድውይ ነኝና አቤቱ፥ ማረኝ፤ አጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ።

3 ነፍሴም እጅግ ታወከች፤ አንተም አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው?

4 አቤቱ፥ ተመለስ ነፍሴንም አድናት፥ ስለ ቸርነትህም አድነኝ።

5 በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው?

6 በጭንቀቴ ደክሜያለሁ፤ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ።

7 ዓይኔ ከቍጡ ዕንባ የተነሣ ታወከች፤ ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ አረጀሁ።

8 ዓመፃን የምታደርጉ ሁሉ፥ ከእኔ ራቁ፥ እግዚአብሔር የልቅሶዬን ቃል ሰምቶአልና።

9 እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማኝ፤ እግዚአብሔር ጸሎቴን ተቀበለ።

10 ጠላቶቼ ሁሉ ይፈሩ እጅግም ይጐስቍሉ፤ ወደ ኋላቸው ይመለሱ፥ በፍጥነትም ይፈሩ።


መዝሙር 7

ስለ ብንያማዊ ሰው ስለ ኩዝ ቃል ለእግዚአብሔር የዘመረው የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ አምላኬ፥ በአንተ ታመንሁ፤ ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝና አውጣኝ፥

2 ነፍሴን እንደ አንበሳ ነጥቀው እንዳይሰብሩዋት፥ የሚያድንና የሚታደግ ሳይኖር።

3 አቤቱ አምላኬ፥ እንዲህስ ካደረግሁ፥ ዓመፃም በእጄ ቢኖር፥

4 ክፉ ላደረጉብኝም ክፉን መልሼላቸው ብሆን፥ ጠላቴንም በከንቱ ገፍቼው ብሆን፥

5 ጠላት ነፍሴን ያሳድዳት ያግኛትም፥ ሕይወቴንም በምድር ላይ ይርገጣት፥ ክብሬንም በትቢያ ላይ ያዋርዳት።

6 አቤቱ፥ በመዓትህ ተነሥ፥ በጠላቶቼ ላይ በቍጣ ተነሣባቸው፤ አቤቱ አምላኬ፥ ባዘዝኸው ትእዛዝ ንቃ።

7 የአሕዛብም ጉባኤ ይከብብሃል፥ በእነርሱም ላይ ወደ ከፍታ ተመለስ።

8 እግዚአብሔር በአሕዛብ ይፈርዳል፤ አቤቱ፥ እንደ ጽድቄ ፍረድልኝ፥ እንደ የዋህነቴም ይሁንልኝ።

9 የኃጥኣን ክፋት ይጥፋ፥ ጻድቁን ግን አቅና፤ እግዚአብሔር ልቡናንና ኵላሊትን ይመረምራል።

10 እግዚአብሔር የጽድቅ ጋሻዬ ነው ልበ ቅኖችን የሚያድናቸው።

11 እግዚአብሔር የእውነት ዳኛ ነው፥ ኃይለኛም ታጋሽም ነው፥ ሁልጊዜም አይቈጣም።

12 ባትመለሱ ግን ሰይፉን ይስላል፥ ቀስቱን ገተረ አዘጋጀም፤

13 የሞት መሣርያንም አዘጋጀበት፥ ፍላጻዎቹንም የሚቃጠሉ አደረገ።

14 እነሆ፥ በዓመፃ ተጨነቀ ጉዳትን ፀነሰ ኃጢአትንም ወለደ።

15 ጕድጓድን ማሰ ቈፈረም። ባደረገውም ጕድጓድ ይወድቃል።

16 ጉዳቱ በራሱ ይመለሳል፥ ዓመፃውም በአናቱ ላይ ትወርዳለች።

17 እግዚአብሔርን እንደ ጽድቁ መጠን አመሰግናለሁ፥ ለልዑል እግዚአብሔርም ስም እዘምራለሁ።


መዝሙር 8

ለመዘምራን አለቃ በዋሽንት፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ፥ ምስጋናህ በሰማዮች ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና።

2 ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት።

3 የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፥

4 ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?

5 ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፤ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው።

6 በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፥

7 በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፥

8 የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፥ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ።

9 አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ።


መዝሙር 9

ለመዘምራን አለቃ፤ በሙትላቤን፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ።

2 በአንተ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትንም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ።

3 ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፥ ይሰናከላሉ ከፊትህም ይጠፋሉ።

4 ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤ ጽድቅን እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ።

5 አሕዛብን ገሠጽህ፥ ዝንጉዎችንም አጠፋህ፥ ስማቸውንም ለዘላለም ደመሰስህ።

6 ጠላቶች በጦር ለዘላለም ጠፉ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረስህ፥ ዝክራቸውም በአንድነት ጠፋ።

7 እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ይኖራል፥ ዙፋኑንም ለመፍረድ አዘጋጀ፤

8 እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳታል፥ አሕዛብንም በቅንነት ይዳኛቸዋል።

9 እግዚአብሔርም ለድሆች መጠጊያ ሆናቸው፥ እርሱም በመከራቸው ጊዜ ረዳታቸው ነው።

10 ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ፥ አቤቱ፥ የሚሹህን አትተዋቸውምና።

11 በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፥ በአሕዛብም መካከል አደራረጉን ንገሩ፤

12 ደማቸውን የሚመራመር እርሱ አስቦአልና፥ የድሆችንም ጩኸት አልረሳምና።

13 አቤቱ፥ እዘንልኝ፥ ጠላቶቼም የሚያመጡብኝን መከራ እይ፥ ከሞት ደጆች ከፍ ከፍ የምታደርገኝ፤

14 ምስጋናውን ሁሉ እናገር ዘንድ፤ በጽዮን ልጅ በደጆችዋ በማዳንህ ደስ ይለኛል።

15 አሕዛብ በሠሩት ጕድጓድ ወደቁ፥ በዚያችም በሸሸጓት ወጥመድ እግራቸው ተጠመደች።

16 እግዚአብሔር ፍርድን በማድረግ የታወቀ ነው፤ ኃጢአተኛው በእጆቹ ሥራ ተጠመደ።

17 ኃጢአተኞች ወደ ሲኦል ይመለሳሉ፥ እግዚአብሔርን የሚረሱ አሕዛብም ሁሉ።

18 ድሀ ለዘላለም አይረሳምና፥ የችግረኞችም ተስፋቸው ለዘላለም አይጠፋም።

19 አቤቱ፥ ተነሥ፤ ሰውም አይበርታ፥ አሕዛብም በፊትህ ይፈረድባቸው።

20 አቤቱ፥ ፍርሃትን በላያቸው ጫንባቸው፤ አሕዛብ ሰዎች እንደ ሆኑ ይወቁ።


መዝሙር 10

1 አቤቱ፥ ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራም ጊዜ ለምን ትሰወራለህ?

2 በኃጢአተኛ ትዕቢት ድሀ ይናደዳል፤ ባሰቡት ተንኰላቸው ተጠመዱ።

3 ኃጢአተኛ በነፍሱ ፈቃድ ይወደሳልና፥ ዓመፀኛም ይባርካል።

4 ኃጢአተኛ እግዚአብሔርን አበሳጨው፥ እንደ ቍጣውም ብዛት አይመራመረውም በእርሱ ፊት እግዚአብሔር የለም።

5 መንገዱ ሁሉ የረከሰ ነው፥ ፍርድህም በፊቱ የፈረሰ ነው፥ ጠላቶችንም ሁሉ ይገዛቸዋል።

6 በልቡ ይላል። ለልጅ ልጅ አልታወክም ክፉም አያገኘኝም።

7 አፉ መርገምንና ሽንገላን ተንኰልን የተመላ ነው፤ ከምላሱ በታች ጉዳትና መከራ ነው።

8 በመንደሮች መሸመቅያ ይቀመጣል ንጹሓንን በስውር ይገድል ዘንድ፤ ዓይኖቹም ወደ ድኃ ይመለከታሉ።

9 እንደ አንበሳ በችፍግ ዱር በስውር ይሸምቃል፤ ድሀውን ለመንጠቅ ያደባል፤ ድሀውን ይነጥቀዋል በአሽክላውም ይስበዋል።

10 ድሀ ይዋረዳል፥ ይጐብጣል፤ በኃያላኑም እጅግ ይወድቃል።

11 በልቡም ይላል። እግዚአብሔር ረስቶኛል፤ ፈጽሞም እንዳያይ ፊቱን ሰወረ።

12 አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ተነሥ እጅህም ከፍ ከፍ ትበል፤ ድሆችን አትርሳ።

13 ኃጢአተኛ ስለ ምን እግዚአብሔርን አስቈጣው? በልቡ። አይመራመረኝም ይላልና።

14 አየኸው፥ አንተ ክፋትንና ቍጣን ትመለከታለህና በእጅህ ፍዳውን ለመስጠት፤ ድሀ ራሱን ለአንተ ይተዋል፥ ለድሀ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ።

15 የኃጢአተኛንና የክፉን ክንድ ስበር፥ የኃጢአቱንም ብድራት ክፈል ሌላ እስከማይገኝ ድረስ።

16 እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ አሕዛብ ከምድሩ ይጠፋሉ።

17 እግዚአብሔር የድሆችን ምኞት ሰማ፥ ጆሮውም የልባቸውን አሳብ አደመጠች፥

18 ፍርዱ ለድሀ አደግና ለችግረኛ ይደረግ ዘንድ፥ ሰዎች በምድር ላይ አፋቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ እንዳይደግሙ።


መዝሙር 11

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 በእግዚአብሔር ታመንሁ፤ ነፍሴን። እንደ ወፍ ወደ ተራሮች ተቅበዝበዢ እንዴት ትሉአታላችሁ?

2 ኃጢአተኞች እነሆ ቀስታቸውን ገትረዋልና፥ ፍላጻቸውንም በአውታር አዘጋጅተዋልና፥ ልበ ቅኖችን በስውር ይነድፉ ዘንድ።

3 አንተ የሠራኸውን እነሆ እነርሱ አፍርሰዋልና፤ ጻድቅ ግን ምን አደረገ?

4 እግዚአብሔር በተቀደሰው መቅደሱ ነው፤ እግዚአብሔር፥ ዙፋኑ በሰማይ ነው፤ ዓይኖቹ ወደ ድሃ ይመለከታሉ፥ ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ።

5 እግዚአብሔር ጻድቅንና ኅጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል።

6 ወጥመድ በኅጥኣን ላይ ያዘንባል እሳትና ዲን ዐውሎ ነፋስም የጽዋቸው እድል ፈንታ ነው።

7 እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና፥ ጽድቅንም ይወድዳል፤ ቅንነት ግን ፊቱን ታየዋለች።


መዝሙር 12

ለመዘምራን አለቃ፥ ስለ ስምንተኛ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ አድነኝ፤ ደግ ሰው አልቆአልና፥ ከሰው ልጆችም መተማመን ጐድሎአልና።

2 እርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፤ በሽንገላ ከንፈር ሁለት ልብ ሆነው ይናገራሉ።

3 የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል፥ ታላቅ ነገርን የምትናገረውን ምላስ፤

4 ምላሳችንን እናበረታለን፤ ከንፈራችን የእኛ ነው፥ ጌታችን ማን ነው? የሚሉትን።

5 ስለ ድሆች መከራ፥ ስለ ችግረኞች ጩኸት እግዚአብሔር። አሁን እነሣለሁ ይላል፤ መድኃኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ።

6 በምድር ላይ እንደ ተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር። የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው።

7 አቤቱ፥ አንተ ጠብቀን፥ ከዚህችም ትውልድ ለዘላለም ታደገን።

8 በሰው ልጆች ዘንድ ምናምንቴ ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ክፉዎች በዙሪያው ሁሉ ይመላለሳሉ።


መዝሙር 13

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ? እስከ መቼስ ፊትህን ከእኔ ትሰውራለህ?

2 እስከ መቼ በነፍሴ እመካከራለሁ? ትካዜስ እስከ መቼ ሁልጊዜ ይሆናል? እስከ መቼ ጠላቴ በላዬ ይጓደዳል?

3 አቤቱ አምላኬ፥ እየኝ ስማኝም፤ ጠላቴ። አሸነፍሁት እንዳይል፥

4 የሚያስጨንቁኝም እኔ ብናወጥ ደስ እንዳይላቸው፥ ለሞትም እንዳልተኛ ዓይኖቼን አብራ።

5 እኔ ግን በቸርነትህ ታመንሁ፥ ልቤም በመድኃኒትህ ደስ ይለዋል።

6 የረዳኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፥ ለልዑል እግዚአብሔር ስምም እዘምራለሁ።


መዝሙር 14

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 ሰነፍ በልቡ። አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጐስቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም።

2 የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ።

3 ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም።

4 ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፥ በምላሳቸው ሸነገሉ፤

5 ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ፤ አፋቸው መርገምንና መራራን ተሞልቶአል፤

6 ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፤ ጥፋትና ጕስቍልና በመንገዳቸው አለ፥ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና፤ እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም።

7 ሕዝቤን እንደ እንጀራ የሚበሉ ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ በውኑ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም።

8 በዚያ በታላቅ ፍርሃት እጅግ ፈሩ፥ እግዚአብሔር በጻድቃን ትውልድ ዘንድ ነውና።

9 የድሆችን ምክር አሳፈራችሁ፥ እግዚአብሔር ግን ተስፋቸው ነው።

10 ከጽዮን መድኃኒትን ለእስራኤል ማን ይሰጣል? እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ ያዕቆብ ደስ ይለዋል፥ እስራኤልም ሐሤት ያደርጋል።


መዝሙር 15

የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?

2 በቅንነት የሚሄድ፥ ጽድቅንም የሚያደርግ፥ በልቡም እውነትን የሚናገር።

3 በአንደበቱ የማይሸነግል፥ በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ፥ ዘመዶቹንም የማይሰድብ።

4 ኃጢአተኛ በፊቱ የተናቀ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር፥ ለባልንጀራው የሚምል የማይከዳም።

5 ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፥ በንጹሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል። እንዲህ የሚያደርግ ለዘላለም አይታወክም።


መዝሙር 16

የዳዊት ቅኔ።

1 አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና ጠብቀኝ።

2 እግዚአብሔርን። አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም።

3 ፈቃድህ ሁሉ በምድር ባሉት ቅዱሳንና ክቡራን ላይ ነው።

4 ወደ ሌላ ለሚፋጠኑት መከራቸው ይበዛል፤ የቍርባናቸውን ደም እኔ አላፈስሰውም፥ ስማቸውንም በከንፈሬ አልጠራም።

5 እግዚአብሔር የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው፥ ዕጣዬንም የምታጠና አንተ ነህ።

6 ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ፥ ርስቴም ተዋበችልኝ።

7 የመከረኝን እግዚአብሔርን እባርካለሁ፤ ደግሞም በሌሊት ኵላሊቶቼ ይገሥጹኛል።

8 ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም።

9 ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤

10 ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም።

11 የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሐ አለ።


መዝሙር 17

የዳዊት ጸሎት።

1 አቤቱ፥ ጽድቄን ስማ ጩኸቴንም አድምጥ፤ በተንኰለኛም ከንፈር ያልሆነውን ጸሎቴን አድምጥ።

2 ፍርዴ ከፊትህ ይውጣ፥ ዓይኖችህም በቅንነት ይዩ።

3 ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጐበኘኸኝ፤ ፈተንኸኝ፥ ምንም አላገኘህብኝም።

4 የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፤ ስለ ከንፈሮችህ ቃል ጭንቅ የሆኑ መንገዶችን ጠበቅሁ።

5 እግሮች እንዳይናወጡ አረማመዴን በመንገድህ አጽና።

6 አቤቱ፥ ሰምተኸኛልና ወደ አንተ ጠራሁ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ቃሌንም ስማ።

7 የሚያምኑህን ከሚቃወሙ በቀኝህ የምታድናቸው፥ ቸርነትህን ድንቅ አድርገህ ግለጠው።

8 እንደ ዓይን ብሌን ጠብቀኝ፥ በክንፎችህ ጥላ ሰውረኝ፥

9 ከሚያስጨንቁኝ ከኃጢአተኞች፥ ነፍሴንም ከሚከብቡአት ከጠላቶቼ።

10 አንጀታቸውን በስብ ቋጠሩ፥ በአፋቸውም ትንቢትን ተናገሩ።

11 አሁንም እርምጃችንን ከበቡ፤ ዓይናቸውን ወደ ምድር ዝቅ ዝቅ አደረጉ።

12 እርሱ ንጥቂያን እንደሚናፍቅ አንበሳ ተሸጕጦም እንደሚኖር እንደ አንበሳ ደቦል ነው።

13 አቤቱ፥ ተነሥ፤ ቀድመህ ወደ ታች ጣለው፤ ነፍሴን ከኃጢአተኛ በሰይፍህ አድናት።

14 አቤቱ፥ ከሰዎች፥ እድል ፈንታቸው በሕይወታቸው ከሆነች ከዚህ ዓለም ሰዎች በእጅህ አድነኝ፤ ከሰወርኸው መዝገብህ ሆዳቸውን አጠገብህ፤ ልጆቻቸው ብዙ ናቸው የተረፋቸውንም ለሕፃናቶቻቸው ያተርፋሉ።

15 እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ።


መዝሙር 18

ለመዘምራን አለቃ ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ እግዚአብሔር ባዳነው ቀን በዚህ መዝሙር ቃል ለእግዚአብሔር የተናገረው የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር። እንዲህም አለ።

1 አቤቱ ጕልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ።

2 እግዚአብሔር ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፥ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው።

3 ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፥ ከጠላቶቼም እድናለሁ።

4 የሞት ጣር ያዘኝ፥ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፤

5 የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድም ደረሰብኝ።

6 በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ።

7 ምድርም ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም፥ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ።

8 ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከፊቱም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ።

9 ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም፥ ጨለማ ከእግሩ በታች ነበረ።

10 በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ በረረ።

11 መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፤ በዙሪያውም ድንኳኑ፤ በደመናት ውስጥ የጨለማ ውኃ ነበረ።

12 በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም አለፉ።

13 እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ።

14 ፍላጻውን ላከ በተናቸውም፤ መብረቆችን አበዛ አወካቸውም።

15 አቤቱ፥ ከዘለፋህ ከመዓትህም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የውኆች ምንጮች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ።

16 ከላይ ሰደደ ወሰደኝም፥ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ።

17 ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና።

18 በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ሆነ።

19 ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፤ ወድዶኛልና አዳነኝ።

20 እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል።

21 የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁም።

22 ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፥ ሥርዓቱንም ከፊቴ አላራቅሁም።

23 በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ።

24 እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ።

25 ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤

26 ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ።

27 አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ።

28 አንተ መብራቴን ታበራለህና፤ እግዚአብሔር አምላኬ ጨለማዬን ያበራል።

29 በአንተ ከጥፋት እድናለሁና በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁ።

30 የአምላኬ መንገድ ፍጹም ነው፥ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው።

31 ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችን በቀር አምላክ ማን ነው?

32 ኃይልን የሚያስታጥቀኝ መንገዴንም የሚያቃና፥

33 እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች የሚያረታ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው።

34 እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፥ በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለሁ።

35 ለደኅንነቴም መታመኛን ሰጠኸኝ፥ ቀኝህም ትረዳኛለች፥ ትምህርትህም ለዘላለም ታጠናኛለች፥ ተግሣጽህም ታስተምረኛለች።

36 አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም።

37 ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ እይዛቸዋለሁም፥ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም።

38 አስጨንቃቸዋለሁ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ።

39 ለሰልፍም ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፤ በበላዬ የቆሙትን ሁሉ በበታቼ ታስገዛቸዋለህ።

40 የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው።

41 ጮኹ የሚረዳቸውም አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ አልሰማቸውም።

42 እንደ ትቢያ በነፋስ ፊት እፈጫቸዋለሁ፥ እንደ አደባባይም ጭቃ እረግጣቸዋለሁ።

43 ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፥ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፥ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል።

44 በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ፤ የባዕድ ልጆች ደለሉኝ።

45 የባዕድ ልጆች አረጁ፥ በመንገዳቸውም ተሰናከሉ።

46 እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ አምላኬም ቡሩክ ነው፥ የመድኃኒቴም አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።

47 በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ አሕዛብን በበታቼ ያስገዛልኛል።

48 ከጠላቶቼ የሚታደገኝ እርሱ ነው፤ በእኔም ላይ ከቆሙ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፥ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ።

49 አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ።

50 የንጉሡን መድኃኒት ታላቅ ያደርጋል፥ ቸርነቱንም ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይሰጣል።


መዝሙር 19

ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር።

1 ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።

2 ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች።

3 ነገር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም።

4 ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።

5 በእነርሱም ውስጥ የፀሐይን ድንኳን አደረገ፥ እርሱም እንደ ሙሽራ ከእልፍኙ ይወጣል፤ እንደ አርበኛ በመንገዱ ለመሮጥ ደስ ይለዋል።

6 አወጣጡ ከሰማያት ዳርቻ ነው፥ ዙረቱም እስከ ዳርቻቸው ነው፤ ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም።

7 የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል።

8 የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፥ ዓይንንም ያበራል።

9 የእግዚአብሔር ፍርሃት ንጹሕ ነው፤ ለዘላለም ይኖራል፤ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ነው።

10 ከወርቅና ከክቡር ዕንቍ ይልቅ ይወደዳል፤ ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል።

11 ባሪያህ ደግሞ ይጠብቀዋል፤ በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል።

12 ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ።

13 የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ።

14 አቤቱ፥ ረድኤቴ መድኃኒቴም፥ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን።


መዝሙር 20

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 በመከራ ቀን እግዚአብሔር ይስማህ፤ የያዕቆብ አምላክ ስም ያቁምህ።

2 ከመቅደሱ ረድኤትን ይላክልህ፥ ከጽዮንም ያጥናህ።

3 ቍርባንህን ሁሉ ያስብልህ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህን ያለምልምልህ።

4 እንደ ልብህ ይስጥህ ፈቃድህንም ሁሉ ይፈጽምልህ።

5 በማዳንህ ደስ ይለናል፤ በአምላካችን ስም ከፍ ከፍ እንላለን፤ ልመናህን ሁሉ እግዚአብሔር ይፈጽምልህ።

6 እግዚአብሔር የቀባውን እንዳዳነው ዛሬ አወቅሁ፤ ከሰማይ መቅደሱ ይመልስለታል፤ በቀኙ ብርታት ማዳን።

7 እነዚያ በሰረገላ እነዚያም በፈረስ ይታመናሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ከፍ ከፍ እንላለን።

8 እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ፤ እኛ ግን ተነሣን፥ ጸንተንም ቆምን።

9 አቤቱ፥ ንጉሥን አድነው፥ በጠራንህም ቀን ስማን።


መዝሙር 21

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል፤ በማዳንህ እጅግ ሐሤትን ያደርጋል።

2 የልቡን ፈቃድ ሰጠኽው፥ የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም።

3 በበጎ በረከት ደርሰህለታልና፤ ከክቡር ዕንቍ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ።

4 ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም፥ ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ።

5 በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው፤ ክብርንና ምስጋናን ጨመርህለት።

6 የዘላለም በረከትን ሰጥተኸዋልና። በፊትህም ደስታ ደስ ታሰኘዋለህ።

7 ንጉሥ በእግዚአብሔር ተማምኖአልና፥ በልዑልም ምሕረት አይናወጥም።

8 እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታግኛቸው፥ ቀኝህም የሚጠሉህን ሁሉ ታግኛቸው።

9 በተቈጣህም ጊዜ እንደ እሳት እቶን አድርጋቸው፤ እግዚአብሔር በቍጣው ያጠፋቸዋል፥ እሳትም ትበላቸዋለች።

10 ፍሬአቸውን ከምድር ዘራቸውንም ከሰው ልጆች ታጠፋለህ።

11 ክፋትን በአንተ ላይ ዘርግተዋልና፥ የማይቻላቸውንም ምክር አሰቡ።

12 ወደ ኋላቸው ትመልሳቸዋለህ፤ ፍላጻን በፊታቸው ላይ ታዘጋጃለህ።

13 አቤቱ፥ በኃይልህ ከፍ ከፍ በል፤ ጽናትህንም እናመሰግናለን እንዘምርማለን።


መዝሙር 22

ለመዘምራን አለቃ ስለ ንጋት ኃይል፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ቃል ሩቅ ነህ።

2 አምላኬ፥ በቀን ወደ አንተ እጠራለሁ፥ አልመለስህልኝም፤ በሌሊትም እንኳ ዕረፍት የለኝም።

3 በእስራኤል የተመሰገንህ አንተ ግን በቅድስና ትኖራለህ።

4 አባቶቻችን አንተን ተማመኑ፥ ተማመኑ አንተም አዳንሃቸው።

5 ወደ አንተ ጮኹ አመለጡም፥ አንተንም ተማመኑ አላፈሩም።

6 እኔ ግን ትል ነኝ ሰውም አይደለሁም፤ የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ።

7 የሚያዩኝ ሁሉ ይላገዱብኛል፤ ራሳቸውን እየነቀነቁ በከንፈሮቻቸው እንዲህ ይላሉ።

8 በእግዚአብሔር ተማመነ፥ እርሱንም ያድነው፤ ቢወድደውስ ያድነው።

9 አንተ ግን ከሆድ አውጥተኸኛልና፥ በእናቴ ጡት ሳለሁም በአንተ ታመንሁ።

10 ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ።

11 ጭንቀት ቀርባለችና የሚረዳኝም የለምና ከእኔ አትራቅ።

12 ብዙ በሬዎች ከበቡኝ፥ የሰቡትም ፍሪዳዎች ያዙኝ፤

13 እንደ ነጣቂና እንደሚጮኽ አንበሳ በላዬ አፋቸውን ከፈቱ።

14 እንደ ውኃ ፈሰስሁ፤ አጥንቶቼም ሁሉ ተለያዩ፤ ልቤ እንደ ሰም ሆነ፥ በአንጀቴም መካከል ቀለጠ።

15 ኃይሌ እንደ ገል ደረቀ፥ በጕሮሮዬም ምላሴ ተጣጋ፥ ወደ ሞትም አሸዋ አወረድኸኝ።

16 ብዙ ውሾች ከብበውኛልና፤ የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ፤ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ።

17 አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ፤ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም።

18 ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።

19 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ፤ አንተ ጕልበቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

20 ነፍሴን ከሰይፍ አድናት፥ ብቻነቴንም ከውሾች እጅ።

21 ከአንበሳ አፍ አድነኝ፥ ብቻነቴንም አንድ ቀንድ ካላቸው።

22 ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፥ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ።

23 እግዚአብሔርን የምትፈሩ፥ አመስግኑት፤ የያዕቆብ ዘር ሁላችሁ፥ አክብሩት፥ የእስራኤልም ዘር ሁላችሁ፥ ፍሩት።

24 የችግረኛን ችግር አልናቀምና፥ ቸልም አላለምና፤ ፊቱንም ከእኔ አልሰወረምና፥ ነገር ግን ወደ እርሱ በጮኽሁ ጊዜ ሰማኝ።

25 በታላቅ ጉባኤ ምስጋናዬ ከአንተ ዘንድ ነው። እርሱን በሚፈሩት ፊት ስእለቴን እሰጣለሁ።

26 ችግረኞች ይበላሉ፥ ይጠግቡማል፤ እግዚአብሔርንም የሚሹት ያመሰግኑታል፤ ልባቸውም ለዘላለም ሕያው ይሆናል።

27 የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሱ፤ የአሕዛብ ነገዶች ሁሉ በፊቱ ይሰግዳሉ።

28 መንግሥት ለእግዚአብሔር ነውና፥ እርሱም አሕዛብን ይገዛል።

29 የምድር ደንዳኖች ሁሉ ይበላሉ ይሰግዳሉም፤ ወደ መሬት የሚወርዱት ሁሉ በፊቱ ይንበረከካሉ፤ ነፍሴም ስለ እርሱ በሕይወት ትኖራለች።

30 ዘሬ ይገዛለታል፤ የምትመጣው ትውልድ ለእግዚአብሔር ትነግረዋለች፤

31 ጽድቁንም ለሚወለደው ሕዝብ፥ እግዚአብሔር ያደረገውን ጽድቁን፥ ይነግራሉ።


መዝሙር 23

የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም።

2 በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል።

3 ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ።

4 በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል።

5 በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ፥ ጽዋዬም የተረፈ ነው።

6 ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ በእግዚአሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ።


መዝሙር 24

በመጀመሪያ ሰንበት የዳዊት መዝሙር።

1 ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ።

2 እርሱ በባሕሮች መሥርቶአታልና፥ በፈሳሾችም አጽንቶአታልና።

3 ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል?

4 እጆቹ የነጹ፥ ልቡም ንጹሕ የሆነ፥ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሣ፥ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ።

5 እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ከመድኃኒቱ አምላክም ምሕረትን ይቀበላል።

6 ይህች ትውልድ እርሱን የምትፈልግ ናት፥ የያዕቆብን አምላክ ፊት የምትፈልግ።

7 እናንት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ።

8 ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኃያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰልፍ ኃያል።

9 እናንተ መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ።

10 ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? የጭፍሮች አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ የክብር ንጉሥ ነው።


መዝሙር 25

የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ።

2 አምላኬ፥ አንተን ታመንሁ፤ አልፈር፥ ጠላቶቼ በእኔ አይሣቁብኝ።

3 አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም፤ በከንቱ የሚገበዙ ያፍራሉ።

4 አቤቱ፥ መንገድህን አመልክተኝ፥ ፍለጋህንም አስተምረኝ።

5 አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።

6 አቤቱ፥ ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና።

7 የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፤ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ።

8 እግዚአብሔር ቸር ቅንም ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።

9 ገሮችን በፍርድ ይመራል፥ ለገሮችም መንገድን ያስተምራቸዋል።

10 የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው። ቃል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ።

11 አቤቱ፥ ኃጢአቴ እጅግ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ።

12 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው? በሚመርጠው መንገድ ያስተምረዋል።

13 ነፍሱ በመልካም ታድራለች፥ ዘሩም ምድርን ይወርሳል።

14 እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው ነው፥ ቃል ኪዳኑንም ያስታውቃቸዋል።

15 እርሱ እግሮቼን ከወጥመድ ያወጣቸዋልና ዓይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው።

16 እኔ ብቻዬንና ችግረኛ ነኝና ፊትህን ወደ እኔ አድርግ ማረኝም።

17 የልቤ ችግር ብዙ ነው፤ ከጭንቀቴ አውጣኝ።

18 ድካሜንና መከራዬን እይ፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ።

19 ጠላቶቼ እንደ በዙ እይ፥ የግፍም ጥል ጠልተውኛል።

20 ነፍሴን ጠብቅና አድነኝ፤ አንተን ታምኛለሁና አልፈር።

21 አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና የውሃትና ቅንነት ይጠብቁኝ።

22 አቤቱ፥ እስራኤልን ከመከራው ሁሉ አድነው።


መዝሙር 26

የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ እኔ በየውሃቴ ሄጃለሁና ፍረድልኝ፤ በእግዚአብሔርም አምኛለሁና አልናወጥም።

2 አቤቱ፥ ፍተነኝ መርምረኝም፤ ኵላሊቴንና ልቤን ፍተን።

3 ምሕረትህ በዓይኔ ፊት ነውና፥ በእውነትህም ተመላለስሁ።

4 በከንቱ ሸንጎ አልተቀመጥሁም፥ ከዓመፀኞችም ጋር አልገባሁም።

5 የክፉዎችን ማኅበር ጠላሁ፥ ከዝንጉዎችም ጋር አልቀመጥም።

6 እጆቼን በንጽሕና አጥባለሁ፤ አቤቱ፥ መሠዊያህን እዞራለሁ፥

7 የምስጋናን ድምፅ እሰማ ዘንድ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግር ዘንድ።

8 አቤቱ፥ የቤትህን ስፍራ የክብርህንም ማደሪያ ቦታ ወደድሁ።

9 ከኃጢአተኞች ጋር ነፍሴን፥ ከደም ሰዎችም ጋር ሕይወቴን አታጥፋ።

10 በእጃቸው ተንኰል አለባቸው፥ ቀኛቸውም መማለጃ ተሞልታለች።

11 እኔ ግን በየውሃቴ ሄጃለሁ፤ አድነኝ ማረኝም።

12 እግሮቼ በቅንነት ቆመዋልና፤ አቤቱ፥ በማኅበር አመሰግንሃለሁ።


መዝሙር 27

ሳይቀባ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው?

2 ክፉዎች፥ አስጨናቂዎቼ ጠላቶቼም፥ ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ በቀረቡ ጊዜ፥ እነርሱ ተሰናከሉና ወደቁ።

3 ሠራዊትም ቢሰፍርብኝ ልቤ አይፈራም፤ ሰልፍም ቢነሣብኝ በዚህ እተማመናለሁ።

4 እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።

5 በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና።

6 እነሆ፥ አሁን በዙሪያ ባሉ በጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ ከፍ አደረገ፤ በድንኳኑም የእልልታ መሥዋዕትን ሠዋሁ፥ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ እዘምርለትማለሁ።

7 አቤቱ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን ቃሌን ስማኝ። ማረኝና አድምጠኝ።

8 አንተ ፊቴን እሹት ባልህ ጊዜ። አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ ልቤ አንተን አለ።

9 ፊትህን ከእኔ አትሰውር፥ ተቈጥተህ ከባሪያህ ፈቀቅ አትበል፤ ረዳት ሁነኝ፥ አትጣለኝም፥ የመድኃኒቴም አምላክ ሆይ፥ አትተውኝ።

10 አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ።

11 አቤቱ፥ መንገድህን አስተምረኝ፥ ስለ ጠላቶቼም በቀና መንገድ ምራኝ።

12 የሐሰት ምስክሮችና ዓመፀኞች ተነሥተውብኛልና ለጠላቶቼ ፈቃድ አትስጠኝ።

13 የእግዚአብሔርን ቸርነት በሕያዋን ምድር አይ ዘንድ አምናለሁ።

14 እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።


መዝሙር 28

የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ወደ አንተ እጠራለሁ፤ ዝም ብትለኝ ወደ ጓድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልመስል፥ አንተ አምላኬ፥ ዝም አትበለኝ።

2 ወደ መቅደስህ ማደሪያ እጄን ባነሣሁ ጊዜ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን የልመናዬን ቃል ስማ።

3 ከኃጥኣንና ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነፍሴን አትውሰዳት፤ ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ።

4 እንደ ሥራቸው እንደ አካሄዳቸውም ክፉት ስጣቸው፤ እንደ እጃቸውም ሥራ ስጣቸው፤ ፍዳቸውን ወደ ራሳቸው መልስ።

5 ወደ እግዚአብሔር ሥራ ወደ እጆቹም አደራረግ አላሰቡምና ያፈርሳቸዋል እንጂ አይሠራቸውም።

6 የልመናዬን ቃል ሰምቶኛልና እግዚአብሔር ይመስገን።

7 እግዚአብሔር ኃይሌና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ፤ ሥጋዬም ደስ ይለዋል፥ ፈቅጄም አመሰግነዋለሁ።

8 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይላቸው ነው፥ ለቀባውም የመድኃኒቱ መታመኛ ነው።

9 ሕዝብህን አድን፥ ርስትህንም ባርክ፤ ጠብቃቸው፥ ለዘላለሙም ከፍ ከፍ አድርጋቸው።


መዝሙር 29

ከድንኳን በመውጣት ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 የአምላክ ልጆች ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አምጡ። ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ።

2 የስሙን ክብር ለእግዚአብሔር አምጡ፥ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ።

3 የእግዚአብሔር ድምፅ በውኆች ላይ፥ የክብር አምላክ አንጐደጐደ፥ እግዚአብሔር በብዙ ውኆች ላይ።

4 የእግዚአብሔር ድምፅ በኃይል ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅ በታላቅ ክብር ነው።

5 የእግዚአብር ድምፅ ዝግባን ይሰብራል፤ እግዚአብሔር የሊባኖስን ዝግባ ይቀጠቅጣል።

6 እንደ ጥጃ ሊባኖስን፥ አንድ ቀን እንዳለው አውሬ ልጅ ስርዮንን ያዘልላቸዋል።

7 የእግዚአብሔር ድምፅ የእሳቱን ነበልባል ይቈርጣል።

8 የእግዚአብሔር ድምፅ ምድረ በዳውን ያናውጣል፥ እግዚአብሔር የቃዴስን ምድረ በዳ ያናውጣል።

9 የእግዚአብሔር ድምፅ ዋላዎችን ያጠነክራቸዋል፥ ጫካዎቹንም ይገልጣል፤ ሁሉም በመቅደሱ። ምስጋና ይላል።

10 እግዚአብሔር የጥፋት ውኃን ሰብስቦአል፤ እግዚአብሔር ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይቀመጣል።

11 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይልን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል።


መዝሙር 30

ለቤቱ መመረቅ ምስጋና፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ተቀብለኸኛልና፥ ጠላቶቼንም ደስ አላሰኘህብኝምና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።

2 አቤቱ አምላኬ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ ምሕረትም አደረግህልኝ።

3 አቤቱ፥ ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፥ ወደ ጕድጓድም እንዳልወርድ አዳንኸኝ።

4 ቅዱሳን ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፥ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ።

5 ቍጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፥ ሞገሱ ግን ለሕይወት ዘመን፤ ልቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል።

6 እኔም በደስታዬ። ለዘላለም አልታወክም አልሁ።

7 አቤቱ፥ በፈቃድህ ለሕይወቴ ኃይልን ሰጠሃት፤ ፊትህን መለስህ፥ እኔም ደነገጥሁ።

8 አቤቱ፥ ወደ አንተ ጠራሁ፥ ወደ አምላኬም ለመንሁ።

9 ወደ ጥፋት ብወርድ በደሜ ምን ጥቅም አለ? አፈር ያመሰግንሃልን? እውነትህንም ይናገራልን?

10 እግዚአብሔር ሰማ ማረኝም፤ እግዚአብሔር ረዳቴ ሆነኝ።

11 ክብሬ ትዘምርልህ ዘንድ ዝምም እንዳትል ልቅሶዬን ለደስታ ለወጥህልኝ፥ ማቄን ቀድደህ ደስታንም አስታጠቅኸኝ።

12 አቤቱ አምላኬ፥ ለዘላለም አመሰግንሃለሁ።


መዝሙር 31

ለመዘምራን አለቃ፤ በማድነቅ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ አንተን ታመንሁ፤ ለዘላለም አልፈር፤ በጽድቅህም አድነኝ።

2 ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ፈጥነህም አድነኝ፤ ታድነኝ ዘንድ መታመኛ አምላክና የመጠጊያ ቤት ሁነኝ።

3 አምባዬና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ መንገዴን አቅና ምራኝም።

4 አንተ መታመኛዬ ነህና ከደበቁብኝ ወጥመድ አውጣኝ።

5 በእጅህ ነፍሴን እሰጣለሁ፤ የእውነት አምላክ አቤቱ፥ ተቤዥተኸኛል።

6 ከንቱ ምናምንቴነትን የጠበቁትን ጠላህ፤ እኔ ግን በእግዚአብሔር ታመንሁ።

7 መከራዬን አይተሃልና፥ ነፍሴንም ከጭንቀት አድነሃታልና በምሕረትህ ደስ ይለኛል ሐሤትም አደርጋለሁ።

8 በጠላቴ እጅ አልዘጋኸኝም፥ በሰፊም ስፍራ እግሮቼን አቆምህ።

9 ተቸግሬአለሁና አቤቱ ምራኝ፤ ዓይኔም ከኃዘን የተነሣ ተፈጀች፥ ነፍሴም ሆዴም።

10 ሕይወቴ በኅዘን አልቃለችና፥ ዓመታቴም በልቅሶ ጩኸት፤ ኃይሌ በችግር ደከመ፥ አጥንቶቼም ተነዋወጡ።

11 በጠላቶቼ ዘንድ ተነወርኹ፥ ይልቁንም በጎረቤቶቼ ዘንድ፥ ለሚያውቁኝም ፍርሃት ሆንሁ፤ በሜዳ ያዩኝም ከእኔ ሸሹ።

12 እንደ ሞተ ሰው ከልብ ተረሳሁ፥ እንደ ተበላሸ ዕቃም ሆንሁ።

13 የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁና፤ በዙሪያው ፍርሃት ነበረ፤ በላዬ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ነፍሴን ለመንጠቅ ተማከሩ።

14 አቤቱ፥ እኔ ግን በአንተ ታመንሁ፤ አንተ አምላኬ ነህ አልሁ።

15 ርስቴ በእጅህ ነው፤ ከጠላቶቼ እጅና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ።

16 ፊትህን በባሪያህ ላይ አብራ፥ ስለ ምሕረትህም አድነኝ።

17 አቤቱ፥ አንተን ጠርቻለሁና አልፈር፤ ክፉዎች ይፈሩ በሲኦልም ዝም ይበሉ።

18 በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ።

19 በአንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀሃት ለሚፈሩህም የሰወርሃት፥ ቸርነትህ እንደ ምን በዛች!

20 በፊትህ መጋረጃ ከሰው ክርክር ትጋርዳቸዋለህ፥ በድንኳንህም ከአንደበት ክርክር ትሸፍናቸዋለህ።

21 በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን በእኔ የገለጠ እግዚአብሔር ይመስገን።

22 እኔስ ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፥ በድንጋጤ አልሁ፤ አንተ ግን ወደ አንተ በጮኽሁ ጊዜ የልመናዬን ቃል ሰማኸኝ።

23 ሁላችሁ ቅዱሳኑ፥ እግዚአብሔርን ውደዱት፤ እግዚአብሔር እውነተኞችን ይፈልጋል፥ ትዕቢተኞችንም ፈጽሞ ይበቀላቸዋል።

24 በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ፥ በርቱ ልባችሁም ይጥና።


መዝሙር 32

የዳዊት ትምህርት።

1 መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው።

2 እግዚአብሔር በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ምስጉን ነው።

3 ሁልጊዜ ከመጮኼ የተነሣ ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፤

4 በቀንና በሌሊት እጅህ ከብዳብኛለችና፥ እርጥበቴም ለበጋ ትኵሳት ተለወጠ።

5 ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፥ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ።

6 ስለዚህ ቅዱስ ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይለምናል፤ ብዙ የጥፋት ውኃም ወደ እርሱ አይቀርብም።

7 አንተ ለእኔ መሸሸጊያዬ ነህ፥ ከጣርም ትጠብቀኛለህ፤ ከከበቡኝ ታድነኝ ዘንድ ደስታዬ ነህ።

8 አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ።

9 ወደ አንተ እንዳይቀርቡ በልባብና በልጓም ጉንጫቸውን እንደሚለጕሙአቸው፥ ልብ እንደሌላቸው እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ።

10 በኃጢአተኛ ብዙ መቅሠፍት አለበት፤ በእግዚአብሔር የሚታመነውን ግን ምሕረት ይከብበዋል።

11 ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ ሐሤትም አድርጉ፤

ልባችሁም የቀና ሁላችሁ፥ እልል በሉ።


መዝሙር 33

የዳዊት መዝሙር።

1 ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ለቅኖች ምስጋና ይገባል።

2 እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፥ አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት።

3 አዲስ ቅኔም ተቀኙለት፥ በእልልታም መልካም ዝማሬ ዘምሩ፤

4 የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ በእምነት ነውና።

5 ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል፤ የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች።

6 በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤

7 የባሕርን ውኃ እንደ ረዋት የሚሰበስበው፥ ቀላዮችንም በመዝገቦች የሚያኖራቸው።

8 ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን ትፍራው፥ በዓለም የሚኖሩ ሁሉም ከእርሱ የተነሣ ይደንግጡ።

9 እርሱ ተናግሮአልና፥ ሆኑም፤ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም።

10 እግዚአብሔር የአሕዛብን ምክር ያጠፋል፥ የአሕዛብንም አሳብ ይመልሳል።

11 የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘላለም ይኖራል። የልቡም አሳብ ለልጅ ልጅ ነው።

12 እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።

13 እግዚአብሔር ከሰማይ ተመለከተ፥ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ።

14 ከማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩ ሁሉ ተመለከተ፥

15 እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ የሚያስተውል።

16 ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም።

17 ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፤ በኃይሉም ብዛት አያመልጥም።

18 እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በምሕረቱም ወደሚታመኑ፥

19 ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ፥ በራብም ጊዜ ይመግባቸው ዘንድ።

20 ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና።

21 ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና።

22 አቤቱ፥ ምሕረትህ በላያችን ትሁን፥ በአንተ እንደ ታመንን።


መዝሙር 34

ባሳደደው በአቤሜሌክ ፊት መልኩን በለወጠ ጊዜ በሄደም ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፥ ምስጋናውንም ዘወትር በአፌ ነው።

2 ነፍሴ በእግዚአብሔር ትከብራለች፥ ገሮችም ሰምተው ደስ ይላቸዋል።

3 እግዚአብሔርን ከእኔ ጋር ታላቅ አድርጉት፥ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ።

4 እግዚአብሔርን ፈለግሁት መለሰልኝም፥ ከመከራዬም ሁሉ አዳነኝ።

5 ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፥ ፊታችሁም አያፍርም።

6 ይህ ችግረኛ ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው፥ ከመከራውም ሁሉ አዳነው።

7 የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።

8 እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው።

9 የሚፈሩት አንዳችን አያጡምና ቅዱሳኑ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፍሩት።

10 ባለጠጎች ደኸዩ፥ ተራቡም፥ እግዚአብሔርን የሚፈልጉትን ግን ከመልካም ነገር ሁሉ አይጐድሉም።

11 ልጆቼ ኑ፥ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ።

12 ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ?

13 አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ።

14 ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን እሻ ተከተላትም።

15 የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና።

16 መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው።

17 ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው።

18 እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።

19 የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል።

20 እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፥ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም።

21 ኃጢአተኞችን ክፋት ይገድላቸዋል ጻድቃንንም የሚጠሉ ይጸጸታሉ።

22 የባሪያዎቹን ነፍስ እግዚአብሔር ይቤዣል፥ በእርሱም የሚያምኑ ሁሉ አይጸጸቱም።


መዝሙር 35

የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ የሚበድሉኝን በድላቸው፥ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው።

2 ጥሩርና ጋሻ ያዝ፥ እኔንም ለመርዳት ተነሥ።

3 ሰይፍህን ምዘዝ የሚያሳድዱኝንም መንገዳቸውን ዝጋ፤ ነፍሴን። መድኃኒትሽ እኔ ነኝ በላት።

4 ነፍሴን የሚሹ ሁሉ ይፈሩ ይጐስቈሉም፤ ክፉትን በእኔ ላይ የሚያስቡ ይፈሩ ወደ ኋላቸውም ይበሉ።

5 በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ ይሁኑ፥ የእግዚአብሔርንም መልአክ ያስጨንቃቸው።

6 መንገዳቸው ዳጥና ጨለማ ይሁን፥ የእግዚአብሔርም መልአክ ያሳድዳቸው።

7 በከንቱ ያጠፉኝ ዘንድ ወጥመዳቸውን ሸሽገውብኛልና፥ ነፍሴን በከንቱ አበሳጭተዋልና።

8 ያላወቁት ወጥመድ ይምጣባቸው፥ የሸሸጉትም ወጥመድ ይያዛቸው፤ በዚህ ወጥመድ ውስጥ ይውደቁ።

9 ነፍሴ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፥ በማዳኑም ሐሴት ታደርጋለች።

10 አጥንቶቼ ሁሉ እንዲህ ይሉሃል። አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? ችግረኛን ከሚቀማው እጅ፥ ችግረኛንና ድሀውንም ከሚነጥቀው እጅ ታድነዋለህ።

11 የክፋት ምስክሮች ተነሡብኝ፥ የማላውቀውንም በእኔ ላይ ተናገሩ።

12 ስለ በጎ ክፋትን መለሱልኝ፥ ነፍሴንም ልጆችን አሳጡአት።

13 እኔስ እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፥ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤ ጸሎቴም ወደ ብብቴ ተመለሰ።

14 ለወዳጄና ለወንድሜ እንደማደርግ አደረግሁ፤ ለእናቱም እንደሚያለቅስ ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረግሁ።

15 በእኔ ላይ ተሰበሰቡ ደስም አላቸው፤ ግፈኞች በእኔ ላይ ተሰበሰቡ እኔም አላውቅሁም፤ ቀደዱኝ አልተውኝምም።

16 ፈተኑኝ በሣቅም ዘበቱብኝ፥ ጥርሳቸውንም በእኔ ላይ አንቀጫቅጩ።

17 አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ታይልኛለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው ብችነቴንም ከአንበሶች አድናት።

18 አቤቱ፥ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፥ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ።

19 በግፍ የሚጠሉኝ በላዬ ደስ አይበላቸው፥ በከንቱ የሚጣሉኝም በዓይናቸው አይጣቀሱብኝ።

20 ለእኔስ ሰላምን ይናገሩኛልና፥ በቍጣም ሽንገላን ይመክራሉ።

21 አፋቸውንም በእኔ ላይ አላቀቁ፤ እሰይ እሰይ፥ ዓይናችን አየው ይላሉ።

22 አቤቱ፥ አንተ አየኸው፤ ዝም አትበል፤ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ።

23 አምላኬ ጌታዬም፥ ወደ ፍርዴ ተነሥ፥ አቤቱ፥ ፍርዴን አድምጥ።

24 አቤቱ አምላኬ፥ እንደ ጽድቅህ ፍረድልኝ፥ በላዬም ደስ አይበላቸው።

25 በልባቸው። እሰይ እሰይ፥ ነፍሳችንን ደስ አላት አይበሉ፤ ደግሞም። ዋጥነው አይበሉ።

26 በመከራዬ ደስ የሚላቸው ይፈሩ፥ በአንድነትም ይጐስቍሉ፤ በእኔ ላይ የሚታበዩ እፍረትንና ጕስቍልናን ይልበሱ።

27 ጽድቄን የሚወድዱአት ደስ ይበላቸው ሐሴትንም ያድርጉ፤ የባሪያውን ሰላም የሚወድድ እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ዘወትር ይበሉ።

28 ምላሴ ጽድቅህን ሁልጊዜም ምስጋናህን ይናገራል።


መዝሙር 36

ለመዘምራን አለቃ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር።

1 ኃጢአተኛ በራሱ የሚያስት ነገርን ይናገራል፥ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዓይኖቹ ፊት የለም።

2 በአንደበቱ ሸንግሎአልና፤ ኃጢአቱ ባገኘችው ጊዜ ይጠላታል።

3 የአፉ ቃል ግፍና ሽንገላ ነው፤ ማስተዋልን በጎ ማድረግንም ተወ።

4 በመኝታው ጠማማነትን አሰበ፤ መልካም ባልሆነች መንገድ ቆሞአል፤ ክፋትን አይንቃትም።

5 አቤቱ፥ ምሕረትህ በሰማይ ነው፥ እውነትህም ወደ ደመናት ትደርሳለች።

6 ጽድቅህም እንደ እግዚአብሔር ተራሮች፥ ፍርድህም እጅግ ጥልቅ ናት፤ አቤቱ፥ ሰውንና እንስሳን ታድናለህ።

7 አቤቱ፥ ምሕረትህን እንዴት አበዛህ! የሰው ልጆች በክንፎችህ ጥላ ይታመናሉ።

8 ከቤትህ ጠል ይጠጣሉ፥ ከተድላም ፈሳሽ ታጠጣቸዋለህ።

9 የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን።

10 ምሕረትህን በሚያውቁህ ላይ፥ ጽድቅህንም ልባቸው በቀና ላይ ዘርጋ።

11 የትዕቢት እግር አይምጣብኝ፥ የኃጢአተኞችም እጅ አያውከኝ።

12 ዓመፃን የሚያደርጉ ሁሉ ከዚያ ወደቁ፤ ወድቀዋል፥ መቆምም አይችሉም።


መዝሙር 37

የዳዊት መዝሙር።

1 በክፉዎች ላይ አትቅና፥ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፤

2 እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፥ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና።

3 በእግዚአብሔር ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ተቀመጥ፥ ታምነህም ተሰማራ።

4 በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።

5 መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ በእርሱም ታመን፥ እርሱም ያደርግልሃል።

6 ጽድቅህን እንደ ብርሃን። ፍርድህንም እንደ ቀትር ያመጣል።

7 ለእግዚአብሔር ተገዛ ተስፋም አድርገው። መንገድም በቀናችለትና ጥመትን በሚያደርግ ሰው አትቅና።

8 ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና።

9 ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።

10 ገና ጥቂት፥ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም።

11 ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፥ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።

12 ኃጢአተኛ ጻድቁን ይመለካከተዋል፥ ጥርሱንም በእርሱ ላይ ያንገጫግጫል።

13 እግዚአብሔር ይሥቅበታል፥ ቀኑ እንደሚደርስ አይቶአልና።

14 ኃጢአተኞች ሰይፋቸውን መዘዙ፥ ቀስታቸውንም ገተሩ ድሀውንና ችግረኛውን ይጥሉ ዘንድ ልበ ቅኖችንም ይወጉ ዘንድ፤

15 ሰይፋቸው ወደ ልባቸው ይግባ፥ ቀስታቸውም ይሰበር።

16 ለጻድቅ ያለው ጥቂት ከብዙ ከኃጢአተኞች ሀብት ይበልጣል።

17 የኃጥአን ክንድ ትሰበራለችና፤ እግዚአብሔር ግን ጻድቃንን ይደግፋቸዋል።

18 የንጹሓንን መንገድ እግዚአብሔር ያውቃል፥ ርስታቸውም ለዘላለም ነው፤

19 በክፉ ዘመንም አያፍሩም በራብ ዘመንም ይጠግባሉ።

20 ኅጥአን ግን ይጠፋሉ፥ የእግዚአብሔር ጠላቶች በከበሩና ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ እንደ ጢስ ይጠፋሉ።

21 ኃጢአተኛ ይበደራል አይከፍልምም፤ ጻድቅ ግን ይራራል ይሰጣልም።

22 እርሱን የሚባርኩት ምድርን ይወርሳሉና፤ የሚረግሙት ግን ይጠፋሉ።

23 የሰው አካሄድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይጸናል፥ መንገዱንም ይወድዳል።

24 ቢወድቅም ለድንጋፄ አይጣልም፥ እግዚአብሔር እጁን ይዞ ይደግፈዋልና።

25 ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፥ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም።

26 ሁልጊዜ ይራራል ያበድርማል፥ ዘሩም በበረከት ይኖራል።

27 ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፤ ለዘላለምም ትኖራለህ።

28 እግዚአብሔር ፍርዱን ይወድዳልና፥ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል ለንጹሓንም ይበቀልላቸዋል፤ የኅጥኣን ዘር ግን ይጠፋል።

29 ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።

30 የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል፥ አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።

31 የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው፥ በእርምጃውም አይሰናከልም።

32 ኃጢአተኛ ጻድቁን ይመለከተዋል፥ ሊገድለውም ይወድዳል።

33 እግዚአብሔር ግን በእጁ አይተወውም፥ በተፋረደውም ጊዜ አያሸንፈውም።

34 እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፥ መንገዱንም ጠብቅ፥ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ።

35 ኃጥአን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት።

36 ብመለስ ግን አጣሁት፤ ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም።

37 ቅንነትን ጠብቅ፥ ጽድቅንም እይ፤ ለሰላም ሰው ቅሬታ አለውና።

38 በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ። የኃጢአተኞች ቅሬታ ይጠፋል።

39 የጻድቃን መድኃኒታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ በመከራቸውም ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው።

40 እግዚአብሔር ይረዳቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ ከኃጢአተኞችም እጅ ያወጣቸዋል፥ ያድናቸዋል፥ በእርሱ ታምነዋልና።


መዝሙር 38

ለሰንበት መታሰቢያ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ።

2 ፍላጾችህ ወግተውኛልና፥ እጅህንም አክብደህብኛልና።

3 ከቍጣህ የተነሣ ለሥጋዬ ጤና የለውም፤ ከኃጢአቴም የተነሣ ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም።

4 ኃጢአቴ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዶአልና።

5 ከስንፍናዬ የተነሣ ቍስሌ ሸተተ በሰበሰም፤

6 እጅግ ጐሰቈልሁ ተዋረድሁም፥ ሁልጊዜም በትካዜ እመላለሳለሁ።

7 ነፍሴ ስድብን ተሞልታለችና፥ ለሥጋዬም ጤና የላትምና።

8 ታመምሁ፤ እጅግም ተቸገርሁ፥ ከልቤ ውዝዋዜም የተነሣ ጮኽሁ።

9 አቤቱ፥ ፈቃዴ ሁሉ በፊትህ ነው፥ ጭንቀቴም ከአንተ አይሰወርም።

10 ልቤ ደነገጠብኝ፥ ኃይሌም ተወችኝ፥ የዓይኖቼም ብርሃን ፈዘዘ።

11 ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ከቍስሌ ገለል ብለው ቆሙ፥ ዘመዶቼም ርቀው ቆሙ።

12 ነፍሴንም የሚሹአት በረቱብኝ፥ መከራዬንም የሚፈልጉ ከንቱን ተናገሩ፥ ሁልጊዜም በሽንገላ ይመክራሉ።

13 እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቆሮ አፉንም እንደማይከፍት ዲዳ ሆንሁ።

14 እንደማይሰማ ሰው በአፉም ተግሣጽ እንደሌለው ሰው ሆንሁ።

15 አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና፤ አቤቱ አምላኬ፥ አንተ ትሰማኛለህ።

16 ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ እንዳይላቸው ብያለሁና፥ እግሮቼም ቢሰናከሉ ራሳቸውን በእኔ ላይ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ።

17 እኔስ ወደ ማንከስ ቀርቤአለሁና፥ ቍስሌም ሁልጊዜም በፊቴ ነውና።

18 በደሌን እናገራለሁና፥ ስለ ኃጢአቴም እተክዛለሁ።

19 ጠላቶቼ ሕያዋን ናቸው ይበረቱብኝማል፥ በጠማማነትም የሚጠሉኝ በዙ።

20 ጽድቅን ስለ ተከተልሁ፥ በበጎ ፋንታ ክፉን የሚመልሱልኝ ይጠሉኛል።

21 አቤቱ፥ አንተ አትጣለኝ፤ አምላኬ፥ ከኔ አትራቅ።

22 አቤቱ መድኃኒቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።


መዝሙር 39

ለመዘምራን አለቃ፥ ለኤዶታም፤ የዳዊት መዝሙር።

1 በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ።

2 ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፥ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፥ ቍስሌም ታደሰብኝ።

3 ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ፤ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ፥ በአንደበቴም ተናገርሁ።

4 አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ።

5 እነሆ፥ ዘመኖቼን አስረጀሃቸው፤ አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ብቻ ነው።

6 በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጣላ ይመላለሳል፤ ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም።

7 አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው።

8 ከኃጢአቴ ሁሉ አድነኝ፥ ለሰነፎችም ስድብ አታድርገኝ።

9 አንተ ሠርተኸኛልና ዝም አልሁ አፌንም አልከፈትሁም።

10 መቅሠፍትህን ከእኔ አርቅ፥ ከእጅህ ብርታት የተነሣ አልቄአለሁና።

11 በተግሣጽህ ስለ ኃጢአቱ ሰውን ዘለፍኸው፥ ነፍሱም እንደ ሸረሪት ድር ታልቃለች፤ በእውነት ሰው ሁሉ ከንቱ ነው።

12 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ ጩኸቴንም አድምጥ፥ ልቅሶዬንም ቸል አትበለኝ፤ እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና፥ እንደ አባቶችም እንግዳ ነኝና።

13 ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ።


መዝሙር 40

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 ቆይቼ እግዚአብሔር ደጅ ጠናሁት፥ እርሱም ዘንበል አለልኝ ጩኽቴንም ሰማኝ።

2 ከጥፋት ጕድጓድ ከረግረግም ጭቃ አወጣኝ፥ እግሮቼንም በድንጋይ ላይ አቆማቸው፥ አረማመዴንም አጸና።

3 አዲስ ዝማሬን ለአምላካችን ምስጋና በአፌ ጨመረ፤ ብዙዎች ያያሉ ይፈሩማል፥ በእግዚአብሔርም ይታመናሉ።

4 እግዚአብሔርን የታመነ ወደ ትዕቢተኛና ወደ ሐሰተኛ ያልተመለከተ ሰው ምስጉን ነው።

5 አቤቱ አምላኬ፥ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፥ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም፤ ባወራም ብናገርም ከቍጥር ሁሉ በዛ።

6 መሥዋዕትንና ቍርባንን አልወደድህም፤ ሥጋን አዘጋጀህልኝ፤ የሚቃጠለውንና ስለ ኃጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልሻህም።

7 በዚያን ጊዜ አልሁ። እነሆ፥ መጣሁ፤ ስለ እኔ በመጽሐፍ ራስ ተጽፎአል፤

8 አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው።

9 በታላቅ ጉባኤ ጽድቅን አወራሁ፤ እነሆ፥ ከንፈሮቼን አልከለክልም፤ አቤቱ፥ አንተ ጽድቄን ታውቃለህ።

10 እውነትህንም በልቤ ውስጥ አልሰወርሁም፥ ማዳንህንም ተናገርሁ፤ ምሕረትህንና እውነትህን ከታላቅ ጉባኤ አልሰወርሁም።

11 አቤቱ፥ አንተ ምሕረትህን ከእኔ አታርቅ፤ ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ።

12 ቍጥር የሌላት ክፋት አግኝታኛለችና፤ ኃጢአቶቼ ያዙኝ፥ ማየትም ተስኖኛል ከራሴ ጠጕር ይልቅ በዙ፥ ልቤም ተወኝ።

13 አቤቱ፥ ታድነኝ ዘንድ ፍቀድ፤ አቤቱ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

14 ነፍሴን ለማጥፋት የሚወድዱ ይፈሩ፥ በአንድነትም ይጐስቍሉ፤ በእኔ ላይ ክፋትን ሊያደርጉ የሚወድዱ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይጐስቍሉም።

15 እሰይ እሰይ የሚሉኝ እፍረታቸውን ወዲያው ይከፈሉ።

16 አቤቱ፥ የሚፈልጉህ ሁሉ በአንተ ደስ ይበላቸው ሐሤትም ያድርጉ፤ ሁልጊዜ ማዳንህን የሚወድዱ ዘወትር። እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ይበሉ።

17 እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፥ ጌታ ግን ያስብልኛል፤ አንተ ረዳቴና መድኃኒቴ ነህ፤ አምላኬ ሆይ፥ አትዘግይ።


መዝሙር 41

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል።

2 እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፥ ሕያውም ያደርገዋል፥ በምድር ላይም ያስመሰግነዋል፥ በጠላቶቹም እጅ አያሳልፈውም።

3 እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል።

4 እኔስ። አቤቱ ማረኝ፤ አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት አልሁ።

5 ጠላቶቼም በላዬ ክፋትን ይናገራሉ። መቼም ይሞታል ስሙስ መቼ ይሻራል? ይላሉ።

6 እኔን ለማየት ቢገባ ከንቱን ይናገራል፤ ልቡ ኃጢአትን ሰበሰበለት፤ ወደ ሜዳ ይወጣል ይናገራልም።

7 በላዬ በመተባበር ጠላቶቼ ሁሉ ይሾካሾኩብኛል፥ በእኔ ላይም ክፋትን ያስባሉ።

8 ክፉ ነገር መጣበት፤ ተኝቶአል ከእንግዲህ ወዲህ አይነሣም ይላሉ።

9 ደግሞ የሰላሜ ሰው የታመንሁበት እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ።

10 አንተ ግን አቤቱ፥ ማረኝ እመልስላቸውም ዘንድ አስነሣኝ።

11 ጠላቴ እልል አይልብኝምና ስለዚህ እንደ ወደድኸኝ አወቅሁ።

12 እኔን ግን ስለ ቅንነቴ ተቀበልኸኝ፥ በፊትህም ለዘላለም አጸናኸኝ።

13 ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአሔር ይባረክ። አሜን አሜን።


መዝሙር 42

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች ትምህርት።

1 ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች።

2 ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?

3 ዘወትር። አምላክህ ወዴት ነው? ሲሉኝ እንባዬ በቀንና በሌሊት ምግብ ሆነኝ።

4 ይህን ሳስብ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ፈሰሰች፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና፤ በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ።

5 ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ።

6 አምላኬ ሆይ፥ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ታወከች፤ ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር በአርሞንኤምም በታናሹ ተራራ አስብሃለሁ።

7 በፍዋፍዋቴህ ድምፅ ቀላይ ቀላይን ትጠራታለች፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ።

8 እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዝዛል፥ በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል፤ የእኔ ስእለት ለሕይወቴ አምላክ ነው።

9 እግዚአብሔርን። አንተ መጠጊያዬ ነህ፤ ለምን ረሳኸኝ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ? እለዋለሁ።

10 ጠላቶቼ ሁልጊዜ። አምላክህ ወዴት ነው? ባሉኝ ጊዜ አጥንቶቼን እየቀለጣጠሙ ሰደቡኝ።

11 ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ።


መዝሙር 43

የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ፍረድልኝ፥ ከጽድቅ ከራቁ ሕዝብም ክርክሬን ተከራከር፤ ከሸንጋይና ከግፈኛ ሰው አድነኝ።

2 አንተ አምላኬ ኃይሌም፥ ለምን ትተውኛለህ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ?

3 ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ።

4 ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ፥ ጕልማስነቴንም ደስ ወዳሰኛት ወደ አምላኬ እገባለሁ፤ አቤቱ አምላኬ፥ በበገና አመሰግንሃለሁ።

5 ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ።


መዝሙር 44

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች ትምህርት።

1 አቤቱ፥ በጆሮአችን ሰማን፥ አባቶቻችንም በዘመናቸው በቀድሞ ዘመን የሠራኸውን ሥራ ነገሩን።

2 እጅህ አሕዛብን አጠፋች፥ እነርሱንም ተከልህ፤ አሕዛብን ሣቀይኻቸው አሳደድኻቸውም።

3 በሰይፋቸው ምድርን አልወረሱም ክንዳቸውም አላዳናቸው፤ ቀኝህና ክንድህ የፊትህም ብርሃን ነው እንጂ ወድደሃቸዋልና።

4 አምላኬና ንጉሤ አንተ ነህ፤ ለያዕቆብ መድኃኒትንህ እዘዝ።

5 በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን።

6 በቀስቴ የምታመን አይደለሁምና፥ ሰይፌም አያድነኝምና፤

7 አንተ ግን ከጠላቶቻችን አዳንኸን፥ የሚጠሉንንም አሳፈርሃቸው።

8 ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እንከብራለን፥ ስምህንም ለዘላለም እናመሰግናለን።

9 አሁን ግን ጠላኸን አሳፈርኸንም፥ ከሠራዊታችንም ጋር አትወጣም።

10 ከጠላቶቻችንም ፊት ወደ ኋላችን መለስኸን፥ የሚጠሉንም ተነጣጠቁን።

11 እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን።

12 ሕዝብህን ያለ ዋጋ ሰጠህ፥ በመለወጣቸውም ትርፍ የለም።

13 ለጎረቤቶቻችን ስድብ፥ በዙሪያችንም ላሉ መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን።

14 በአሕዛብ ዘንድ ምሳሌ፥ በሕዝብም ዘንድ የራስ መንቀሳቀሻ አደረግኸን።

15 ጕስቍልናዬ ሁልጊዜም በፊቴ ነው፥ የፊቴም እፍረት ሸፈነኝ።

16 ከሚሳደብና ከሚላገድ ቃል የተነሣ፥ ከጠላትና ከቂመኛ ፊት የተነሣ ነው።

17 ይህ ሁሉ በእኛ ላይ ደረሰ፥ አልረሳንህም፥ ኪዳንህንም አልወነጀልንም።

18 ልባችን ወደ ኋላው አልተመለሰም፥ ፍለጋችንም ከመንገድህ ፈቀቅ አላለም፤

19 በክፉ ስፍራ አዋርደኸናልና፥ በሞት ጥላም ሰውረኸናልና።

20 የአምላካችንን ስም ረስተንስ ቢሆን፥ እጃችንንም ወደ ሌላ አምላክ አንሥተንስ ቢሆን፥

21 እግዚአብሔር ይህንን አይመረምርም ነበርን? እርሱ ልብ የሰወረውን ያውቃልና።

22 ስለ አንተ ሁልጊዜም ተገድለናል፥ እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል።

23 አቤቱ፥ ንቃ፤ ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፥ ለዘወትርም አትጣለን።

24 ለምንስ ፊትህን ትሰውራለህ? መከራችንንና ችግራችንንስ ለምን ትረሳለህ?

25 ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጐሳቍላለችና፥ ሆዳችንም ወደ ምድር ተጣብቃለችና።

26 አቤቱ፥ ተነሥና እርዳን፥ ስለ ስምህም ተቤዠን።


መዝሙር 45

ለመዘምራን አለቃ፤ በመለኮቶች፤ የቆሬ ልጆች ትምህርት፤ የፍቅር መዝሙር።

1 ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ፥ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ፤ አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሓፊ ብርዕ ነው።

2 ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል፤ ሞገስ በከንፈሮችህ ፈሰሰ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባረከህ።

3 ኃያል ሆይ፥ በቍንጅናህና በውበትህ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ።

4 ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም አቅና ተከናወን ንገሥም፤ ቀኝህም በክብር ይመራሃል።

5 ኃያል ሆይ፥ ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፥ እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ፥ አሕዛብም በበታችህ ይወድቃሉ።

6 አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘላለም ነው፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው።

7 ጽድቅን ወደድህ ዓመፃንም ጠላህ፤ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክ የደስታ ዘይትን ቀባህ።

8 በልብሶችህ ሁሉ ከርቤና ሽቱ ዝባድም አሉ፤ ከዝሆን ጥርሶች አዳራሽ ደስ ያሰኙሃል።

9 የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።

10 ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤

11 ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውና።

12 የጢሮስ ሴቶች ልጆች እጅ መንሻን ይዘው ይሰግዱለታል። የምድር ባለጠጎች አሕዛብ በፊትህ ይማለላሉ።

13 ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብርዋ ነው፤ ልብስዋ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው።

14 በኋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ፥ ባልንጀሮችዋንም ወደ አንተ ያቀርባሉ፤

15 በደስታና በሐሴት ይወስዱአቸዋል፥ ወደ ንጉሥ እልፍኝም ያስገቡአቸዋል።

16 በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ፥ በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ።

17 ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ፤ ስለዚህ ለዓለምና ለዘላለም አሕዛብ ይገዙልሃል።


መዝሙር 46

ለመዘምራን አለቃ፤ ስለ ምሥጢር፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር።

1 አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።

2 ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።

3 ውኆቻቸው ጮኹ ተናወጡም፥ ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተናወጡ።

4 የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ፤ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ።

5 እግዚአሔር በመካከልዋ ነው አትናወጥም፥ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ይረዳታል።

6 አሕዛብ ተናወጡ መንግሥታትም ተመለሱ፤ እርሱ ቃሉን ሰጠ፥ ምድርም ተንቀጠቀጠች።

7 የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።

8 የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ።

9 እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነት ይሽራል። ቀስትን ይሰብራል፥ ጦርንም ይቈርጣል በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።

10 ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።

11 የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።


መዝሙር 47

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር።

1 አሕዛብ ሁላችሁ፥ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፥ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ።

2 እግዚአብሔር ልዑል ግሩምም ነውና፥ በምድር ሁሉ ላይም ታላቅ ንጉሥ ነውና።

3 አሕዛብን ከእኛ በታች፥ ወገኖችንም ከእግራችን በታች አስገዛልን።

4 ለርስቱ እኛን መረጠን፥ የወደደውን የያዕቆብን ውበት።

5 አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።

6 ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ፤ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ።

7 እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፤ በማስተዋል ዘምሩ።

8 እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ነገሠ፤ እግዚአብሔር በቅድስናው ዙፋን ይቀመጣል።

9 የምድር ኃይለኞች ለእግዚአብሔር ናቸውና የአሕዛብ አለቆች ወደ አብርሃም አምላክ ተሰበሰቡ፤ እርሱንም ከፍ ከፍ አደረጉት።


መዝሙር 48

በሁለተኛ ሰንበት የቆሬ ልጆች፤ የምስጋና መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ትልቅ ነው፤ በአምላካችን ከተማ በተቀደሰ ተራራ ምስጋናው ብዙ ነው።

2 በሰሜን ወገን በመልካም ስፍራ የቆመ የምድር ሁሉ ደስታ የጽዮን ተራራ ነው፤ እርሱም የትልቁ ንጉሥ ከተማ ነው።

3 እግዚአብሔር በአዳራሾችዋ መጠጊያ ሆኖ ይታወቃል።

4 እነሆ፥ ነገሥታት ተከማችተው በአንድነት መጥተዋል።

5 እነርሱስ አይተው ተደነቁ፥ ደነገጡ፥ ታወኩ።

6 መንቀጥቀጥ እንደ ወላድ ምጥ በዚያ ያዛቸው።

7 በኃይለኛ ነፋስ የተርሴስን መርከቦች ትሰብራለህ።

8 እንደ ሰማን እንዲሁ አየን በሠራዊት ጌታ ከተማ፥ በአምላካችን ከተማ፤ እግዚአብሔር ለዘላለም ያጸናታል።

9 አምላክ ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ምሕረትህን ተቀበልን።

10 አምላክ ሆይ፥ እንደ ስምህ እንዲሁም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስጋናህ ነው፤ ቀኝህ ጽድቅን የተሞላች ናት።

11 አቤቱ፥ ስለ ፍርድህ የጽዮን ተራራ ደስ ይበለው፥ የአይሁድም ሴት ልጆች ሐሤት ያድርጉ።

12 ጽዮንን ክበቡአት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ፥ ግንቦችዋንም ቍጠሩ፤

13 በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ፤ አዳራሽዋን አስቡ፤ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ።

14 ለዓለምና ለዘላለም ይህ አምላካችን ነው፥ እርሱም ለዘላለም ይመራናል።


መዝሙር 49

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር።

1 አሕዛብ ሁላችሁ፥ ይህን ስሙ፤ በዓለም የምትኖሩትም ሁላችሁ፥ አድምጡ፤

2 ዝቅተኞችና ከፍተኞች፥ ባለጠጎችና ድሆች በአንድነት።

3 አፌ ጥበብን ይናገራል፥ የልቤም አሳብ ማስተዋልን።

4 ጆሮዬን ወደ ምሳሌ አዘነብላለሁ፥ በበገናም ምሥጢሬን እገልጣለሁ።

5 ኃጢአት ተረከዜን በከበበኝ ጊዜ በክፉ ቀን ለምን እፈራለሁ?

6 በኃይላቸው የሚታመኑ፥ በባለጠግነታቸውም ብዛት የሚመኩ፤

7 ወንድም ወንድሙን አያድንም፥ ሰውም አያድንም፤ ቤዛውን ለእግዚአብሔር አይሰጥም፥

8-9 ለዘላለም እንዲኖር፥ ጥፋትንም እንዳያይ፤ የነፍሳቸው ለውጥ ከብሮአልና፥ ለዘላለምም ቀርቶአልና።

10 ብልሃተኞች እንዲሞቱ፥ ሰነፎችችና ደንቆሮች በአንድነት እንዲጠፉ፥ ገንዘባቸውንም ለሌሎች እንዲተዉ አይቶአል።

11 በልባቸውም ቤታቸው ለዘላለም የሚኖር፥ ማደሪያቸውም ለልጆች ልጅ የሚሆን ይመስላቸዋል፤ በየአገራቸውም ስማቸው ይጠራል።

12 ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም፤ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ።

13 ይህች መንገዳቸው መሰናክላቸው ናት፥ ከእነርሱም በኋላ የሚመጡ በአፋቸው እሺ ይላሉ።

14 እንደ በጎች ወደ ሲኦል የሚሄዱ ናቸው፥ እረኛቸውም ሞት ነው፤ ቅኖችንም በማለዳ ይገዙአቸዋል፥ ውበታቸውም ከመኖሪያቸው ተለይታ በሲኦል ታረጃለች።

15 ነገር ግን እግዚአብሔር ይቀበለኛልና ነፍሴን ከሲኦል እጅ ይቤዣታል።

16 የሰው ባለጠግነት የቤቱም ክብር በበዛ ጊዜ አትፍራ፥

17 በሞተ ጊዜ ከእርሱ ጋር ምንም አይወስድምና፥ ክብሩም ከእርሱ በኋላ አይወርድምና።

18 በሕይወቱ ሳለ ነፍሱን ባርኮአልና ለሰውነቱ መልካም ብታደርግለት ያመሰግንሃል።

19 ሆኖም ወደ አባቶቹ ትውልድ ይወርዳል፤ ለዘላለም ብርሃንን አያይም።

20 አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ።


መዝሙር 50

የአሳፍ መዝሙር።

1 የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፥ ከፀሓይም መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ምድርን ጠራት።

2 ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል።

3 አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊት ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ።

4 በላይ ያለውን ሰማይን ምድርንም በሕዝቡ ለመፍረድ ይጠራል፤

5 ከእርሱ ጋር ለመሥዋዕት ኪዳን የቆሙትን ቅዱሳኑን ሰብስቡለት።

6 ሰማያት ጽድቁን ይናገራሉ፥ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና።

7 ሕዝቤ፥ ስማኝ፥ ልንገርህ፤ እስራኤልም፥ ስማኝ፥ ልመስክርብህ፤ አምላክስ እኔ አምላክህ ነኝ።

8 ስለ ቍርባንህ የምዘልፍህ አይደለሁም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህ ሁልጊዜ በፊቴ ነው።

9 ከቤትህ ፍሪዳን ከመንጋህም አውራ ፍየልን አልወስድም፤

10 የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና።

11 የሰማይን አዕዋፍ ሁሉ አውቃለሁ፥ የምድረ በዳ አራዊትም በእኔ ዘንድ ናቸው።

12 ብራብም ለአንተ አልነግርህም፥ ዓለምና ሞላው የእኔ ነውና።

13 የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን?

14 ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ፤

15 በመከራ ቀን ጥራኝ፥ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ።

16 ኃጢአተኛውን ግን እግዚአብሔር አለው። ለምን አንተ ሕጌን ትናገራለህ? ኪዳኔንም በአፍህ ለምን ትወስዳለህ?

17 አንተስ ተግሣጼን ጠላህ፥ ቃሎቼንም ወደ ኋላህ ጣልህ።

18 ሌባውን ባየህ ጊዜ ከእርሱ ጋር ትሮጥ ነበር እድል ፈንታህንም ከአመንዝሮች ጋር አደረግህ።

19 አፍህ ክፋትን አበዛ፥ አንደበትህም ሽንገላን ተበተበ።

20 ተቀምጠህ ወንድምህን አማኸው፥ ለእናትህም ልጅ ዕንቅፋት አኖርህ።

21 ይህን አድርገህ ዝም አልሁህ፤ እኔ እንደ አንተ እሆን ዘንድ ጠረጠርህ፤ እዘልፍሃለሁ በፊትህም እቆማለሁ።

22 እግዚአብሔርን የምትረሱ እናንተ፥ ይህን አስተውሉ፤ አለዚያ ግን ይነጥቃል የሚያድንም የለም።

23 ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ።