Amharic 2 Timothy


1. በክርስቶስ ኢየሱስ እንደሚሆን የሕይወት ተስፋ፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥

2. ለተወደደው ልጄ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።

3. ሌትና ቀን በልመናዬ ሳላቋርጥ ስለማስብህ እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹሕ ሕሊና የማመልከውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤

4. እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ።

5. በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፥ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቼአለሁ።

6. ስለዚህ ምክንያት፥ እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው፥ እጆቼን በመጫኔ በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታነሣሣ አሳስብሃለሁ።

7. እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።

8. እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤

9. ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥

10. አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።

11. አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።

12. ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።

13. በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤

14. መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።

15. በእስያ ያሉቱ ሁሉ ከእኔ ፈቀቅ እንዳሉ ታውቃለህ፥ ከእነርሱም ፊሎጎስና ሄርዋጌኔስ ናቸው።

16. ጌታ ልሄኔሲፎሩ ቤተ ሰዎች ምሕረትን ይስጥ፥ ብዙ ጊዜ አሳርፎኛልና፤

17. በሰንሰለቴም አላፈረበትም፥ ነገር ግን በሮሜ ባደረ ጊዜ ፈልጎ ፈልጎ አገኘኝ፤

18. በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው፤ በኤፌሶንም እንዴት እንዳገለገለኝ አንተ በደኅና ታውቃለህ።

2 Timothy 2

1. እንግዲህ፥ ልጄ ሆይ፥ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ።

2. ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ።

3. እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፥ አብረኸኝ መከራ ተቀበል።

4. የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም።

5. ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም።

6. የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል።

7. የምለውን ተመልከት፤ ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ።

8. በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤

9. ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።

10. ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስለ ተመረጡት በነገር ሁሉ እጸናለሁ።

11. ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው። ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤

12. ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው፥ እርሱ ደግሞ ይክደናል፤

13. ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።

14. ይህን አሳስባቸው፥ በቃልም እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፥ ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና።

15. የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ።

16. ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፥ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል፤

17. ከእነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው፤

18. እነዚህም። ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል እያሉ፥ ስለ እውነት ስተው፥ የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ።

19. ሆኖም። ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፥ ደግሞም። የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ የሚለው ማኅተም ያለበት የተደላደለ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሞአል።

20. በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፥ እኵሌቶቹም ለክብር፥ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤

21. እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል።

22. ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል።

23. ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ፤

24. የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም።

25. ደግሞም። ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፥ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።

26. ደግሞም። ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፥ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።

2 Timothy 3

1. ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።

2. ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥

3. ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥

4. ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤

5. የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።

6. ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና።

7. ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና።

8. ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ።

9. ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።

10. አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤

11. በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የሆነብኝን የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታም ከሁሉ አዳነኝ።

12. በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።

13. ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፥ እያሳቱና እየሳቱ፥ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ።

14. አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤

15. ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል።

16. የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።

17. የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።

2 Timothy 4

1. በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤

2. ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም።

3. ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።

4. እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።

5. አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም።

6. በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል።

7. መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤

8. ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።

9. በቶሎ ወደ እኔ እንድትመጣ ትጋ፤

10. ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና፥ ወደ ተሰሎንቄም ሄዶአል፤ ቄርቂስም ወደ ገላትያ ቲቶም ወደ ድልማጥያ ሄደዋል፤

11. ሉቃስ ብቻ ከእኔ ጋር አለ። ማርቆስ ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛልና ይዘኸው ከአንተ ጋር አምጣው።

12. ቲኪቆስን ግን ወደ ኤፌሶን ላክሁት።

13. ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖሱንና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ።

14. የናስ አንጥረኛው እስክንድሮስ እጅግ ከፋብኝ፤ ጌታ እንደ ሥራው ይመልስለታል።

15. አንተም ደግሞ ከእርሱ ተጠበቅ፥ የምንናገረውን እጅግ ተቃውሞአልና።

16. በፊተኛው ሙግቴ አንድ ስንኳ አልደረሰልኝም፥ ሁሉም ተዉኝ እንጂ፤ ይህንም አይቍጠርባቸው፤

17. ዳሩ ግን የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ፥ ከአንበሳ አፍም ዳንሁ።

18. ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።

19. ለጵርስቅላና ለአቂላ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ።

20. ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀረ፥ ጥሮፊሞስን ግን ታሞ በሚሊጢን ተውሁት።

21. ከክረምት በፊት እንድትመጣ ትጋ። ኤውግሎስና ጱዴስ ሊኖስም ቅላውዲያም ወንድሞችም ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል።

22. ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስህ ጋር ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።